ደም በመለገስ የተቸገሩ ወገኖች መደገፍ በፈጣሪ ዘንድ ዋጋ ያሰጣል-ቤተክርስቲያኗ - ኢዜአ አማርኛ
ደም በመለገስ የተቸገሩ ወገኖች መደገፍ በፈጣሪ ዘንድ ዋጋ ያሰጣል-ቤተክርስቲያኗ
አዲስ አበባ ግንቦት 8/2012 (ኢዜአ) ደም በመለገስ የተቸገሩ ወገኖች መደገፍ በፈጣሪ ዘንድ ዋጋ የሚያሰጥ መንፈሳዊ ሥራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስታወቀች።
በኮተቤ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን የፍቅረሰላም ዘኮተቤ መንፈሳዊ ማሕበርና የደብሩ ሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ዛሬ ደም ለግሰዋል።
የደብሩ አስተዳዳሪ ቆሞስ አባ ገብረ ሥላሴ ይርሳው በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት በደም እጦት የሚቸገሩ ወገኖችን መደገፍ አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ በፈጣሪ ዘንድ ቦታ አለው።
አባላቱ የደም እጥረትን ለማቃለል የቀረበውን አገራዊ ጥሪን ተቀብለው ያደረጉት የደም ልገሳ ያስመሰግናል ብለዋል።
የአባላቱ አስተባባሪ ወጣት ኃይለአብ በዛብሕ ልገሳው በተለይ ወላድ እናቶችን በደም እጦት ምክንያት ሕይወታቸውን እንዳያጡ ለማድረግ ታስቦ መከናወኑን ገልጿል።
ከደም ለጋሾቹ መካከል አቶ ዳንኤል ሰይፉ ወጣቶች ደም በመለገስ መሳተፍ ወገንን መርዳት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
ወይዘሮ ሕይወት ነጋ የተባሉ የማሕበሩ አባል በበኩላቸው ማሕበሩ ባደረገው ጥሪ ከባለቤታቸው ጋር ሆነው ደም መለገሳቸውን ገልጸዋል ።
የማሕበሩ አባላት ላለፉት 10 ዓመታት በበጎ ሥራዎች መሰማራታቸው በዚሁ ወቅት ተገልጿል።