ቀጥታ፡

በዓለም የወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና አሸናፊ ለመሆን የሚስችል ዝግጅት አድርገናል-ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች

አዲስ አበባ ሰኔ 28/2010 በዓለም ከ20 በታች የወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ወክለው የሚካፈሉ አትሌቶች አሸናፊ ለመሆን የሚያስችል ጥሩ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገለጹ። ከሐምሌ 3 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ለስድስት ተከተታይ ቀናት በፊንላንድ ቴምፔሬ ከተማ የዓለም ከ20 ዓመት በታች የወጣቶች አትሌቲክስ ውድድር ይካሄዳል። በዚህ ውድድር ከ158 ሀገራት የተውጣጡ 1 ሺህ 462  አትሌቶች በተለያዩ ርቀቶች እንደሚካፈሉ የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር(ፊፋ) በድረ-ገጹ ይፋ አድርጓል። ኢትዮጵያም በዚህ ከ400 ሜትር ጀምሮ እስከ 10 ሺህ ሜትር ባሉ ርቀቶችና በእርምጃ ውድድርና በመሰናክል ውድድሮች ትካፈላለች። በዚህ ውድድር የሚካፈሉ 29 አትሌቶች ከያዝነው ወር መጀመሪያ ሳምንት አንስተው በሆቴል ተሰባስበው ዝግጅት እያደረጉ ይገኛሉ። በዚህ ሻምፒዮና  ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ አትሌቶች ሁሉም ለአሸናፊነት የሚመጡ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያን ወክለው  የሚካፈሉ አትሌቶች በዚህ ውድድር የተሻለ ሆኖ በመገኘት  አሸናፊ ለመሆን የሚያስችላቸውን ዝግጅት ማድረጋቸውን ነው የተናገሩት። ከአምስት ወር በፊት በእንግሊዝ በርሚንግሃም ከተማ በተካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ ውድድር በ1 ሺህ 500 ሜትር ለሀገሩ  የወርቅ ሜዳሊያ ያመጣው አትሌት ሳሙኤል ተፈራ በዚህ ውድድርም ባለድል ለመሆን የሚያስችል  ጥሩ ዝግጅት ማድረጉን ነው የሚናገረው። በተመሳሳይ በ10 ሺህ ሜትር የእርምጃ ውድድር የሚካፈለው ዮሀንስ አልጋውና በ10 ሺህ ሜትር ርቀት  ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለውድድር እራሱን እያዘጋጀ ያለው አትሌት በርሄ አረጋዊ በስልጠና ወቅት ሁሉም ነገር እንደተሟለላቸውና  ጥሩ ዝግጅት ማድረጋቸውን  ነው የተናገሩት። የቡድን መሪና የረጅም ርቀት ተወዳደሪ አትሌቶች ዋና አሰልጣኝ ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ በበኩላቸው "በፌዴሬሽኑ በኩል የሚያስልጉ ነገሮች ሁሉ ተሟልተውናል ጥሩ  ዝግጅት እያደረግን ነው" ሲሉ ገልጸዋል። የአትሌቶች የአንድነትና የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውም ጥሩ የሚባል እንደሆነና የቡድን መንፈሱን እንዲያዳብሩ ለማድረግም  እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል ። በዚህ የአትሌቶች ዝግጅት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ስላሴም አትሌቶቹ ልምምድ በሚሰሩበት የአዲስ አበባ ስታዴየም ተግኝቶ አትሌቶችን እያበረታታና ልምዱን እያካፈላቸው እንደነበርም ለመመለከት ችለናል። ኢትዮጵያ በዚህ ውድድር በ10 ሺህ ሜትር፣ በ5 ሺህ፣ በ3 ሺህ ፣ በ1 ሺህ 500፣ በ800  ሜትር፣ በ400 ሜትር፣  በ400 ሜትር ድብልቅ ሪሌ፣  በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል እና በ10 ሺህ ሜትር የእርምጃ ውድድር ትካፈላለች።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም