ግብፅና ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የያዙትን አቋም ለማስተካከል የመሪዎቻቸውን የፖለቲካ ቁርጠኝነት ይጠይቃል - ኢዜአ አማርኛ
ግብፅና ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የያዙትን አቋም ለማስተካከል የመሪዎቻቸውን የፖለቲካ ቁርጠኝነት ይጠይቃል

አዲስ አበባ ግንቦት 8/2012 (ኢዜአ) ግብፅና ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የያዙትን አቋም ለማስተካከል የመሪዎቻቸውን የፖለቲካ ቁርጠኝነት የሚጠይቅ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን ገለጹ።
ኢትዮጵያ ከአገራቱ ጋር መግባባት ላይ እስከምትደርስ ድርድሯን መቀጠል እንዳለባትም ምሁራኑ ጠቁመዋል።
ከኢትዮጵያ ምድር ፈልቆ ለዘመናት የታችኞቹን ተፋሰስ አገራት ብቻ ሲያለማ የቆየው ድንበር ተሻጋሪው ጥቁር አባይ አሁን ላይ ለእናት ምድሩ ብርሃን ለመስጠት ጊዜ በመጠበቅ ላይ ይገኛል።
የአባይን ወንዝ በጥቂቱም ቢሆን ሱዳን ተጠቃሚ በመሆን እስካሁን ብትዘልቅም የአንበሳውን ድርሻ በመውሰድ የምትጠቀመውና በቀጣይም "አባይ ከእኔ ውጭ ነኪ ሊኖረው አይገባም" የሚለው የግብፅ የቅኝ ግዛት እሳቤ አሁንም ቀጥሏል።
ግብፅ ከሩዋንዳና ብሩንድ ተራሮች ተንደርድሮ የሚወርደውን ነጭ አባይና ከኢትዮጵያ እንብርት የሚፈልቀውን ጥቁር አባይ ጠቅልላ በመጠቀም ለዘመናት ዘልቃለች።
ካይሮ ላይ በሰፊው ተንጣሎ የሚገኘውን የአባይ ውሃ ግብፅ ለመስኖ፣ ለዓሳ ምርት፣ ለኤሌክትሪክና የቱሪዝም ሃብት አድርጋ ትጠቀምበታለች።
ግብፅ በአባይ ወንዝ ላይ 5 ሺህ 250 ስኩየር ኪሎ ሜትር የሚያካልልውን እንዲሁም 550 ኪሎ ሜትር የሚረዝመውን ሰው ሰራሽ (የናስር) ሃይቅ በመገንባት ውሃውን እንዳሻት ትጠቀምበታልች።
የአባይን 86 በመቶ የውሃ ድርሻ የምታበረክተው ኢትዮጵያ ግን የበይ ተመልካች እንጂ ተጠቃሚ ሳትሆን እስካሁን ዘልቃለች።
ኢትዮጵያውያ ከውሃው ለዜጎቿ ብርሃን ለማመንጨት ከ9 ዓመታት በፊት የግድብ ግንባታ ጀምራ 73 በመቶ ክንውን ላይ የደረሰች ቢሆንም ግብፅ ''አባይ የግሌ በመሆኑ ማንም ሊነካው አይገባም'' የሚለውን አቋሟን ቀጥላበታለች።
ሆኖም ኢትዮጵያ በሌሎች ላይ ጉዳት በማያደርስ መልኩ በፍትሃዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም የተፈጥሮ ሃብቷን የመልማት መብቷን መጋፋት ተቀባይነት አይኖረውም ይላሉ የዘረፉ ምሁራን።
የብሔራዊ ኤክስፐርቶች ፓናል ሰብሳቢና የሦስትዮሽ ድርድር ኮሚቴ አባል ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው እንደሚሉት እኤአ በ2015 ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በመሪዎቻቸው ካርቱም ላይ በግድቡ ውሃ አሞላል ላይ የመርህ-ስምምነት ተፈራርመዋል።

በዚህ ስምምነት ሶስቱ አገሮች በግድቡ ውሃ አሞላልና እና አለቃቀቅ ላይ መግባባት ላይ መድረሳቸውንም ያስታውሳሉ።
የምስራቅ ናይል ቴክኒካል አህጉራዊ ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ፈቅ አህመድ ነጋሽ እንደሚሉት በፍትሃዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም ህግ መሰረት ኢትዮጵያ የታችኞቹ የአባይ ተፋሰስ አገሮች ላይ ጉዳት በማያደርስ መልኩ እንደምትጠቀም በተለያዩ ጊዜያቶች አረጋግጣለች።

ግድቡ ሃይል ማመንጨት ሲጀምር የኢትዮጵያን ሃይል የማመንጨት አቅም በ300 ፐርሰንት ማሳደግ የሚያስችል ሲሆን የግብጽን ሃይል ማመንጨት አቅም በ0 ነጥብ 07 በመቶ ብቻ ሊቀንስ ይችላል ነው ያሉት።
የታችኞቹ ተፋሰስ አገሮች የጎርፍና የደለል ስጋታቸውን ከማስወገድ ጀምሮ ተጨማሪ ውሃ እንዲያገኙ የግድቡ ግንባታ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው ይህም የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርግ እንጂ የሚጎዳ አለመሆኑን አብራርተዋል።
አገሮቹ ምንም እንኳ እውነታውን ቢረዱትም በተለይ ግድቡ ውሃ መሙላት ደረጃ ላይ ሲደርስ በኢትዮጵያ ላይ ጫና መፍጠራቸው አይቀሬ መሆኑን ያነሳሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህግ ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ደረጀ ዘለቀ ግብጽና ሱዳን የአባይን ውሃ እኔ ብቻ ልጠቀም የሚል የቆየ አቋማቸውን በቀላሉ ማስቀየር አዳጋች መሆኑን ይስማማሉ።

አገራቱ ኢትዮጵያን የአባይ ውሃ ህጋዊ ተጠቃሚ መሆኗን ሳይረዱ ቀርተው ሳይሆን በወንዙ ለይ በያዙት የተሳሳተ የፖለቲካ አመለካከት መሆኑን በመግለጽ።
አገራቱ በተለይ በህዳሴ ግድቡ ላይ የያዙትን የተሳሳተ አቋም ማስተካከል የሚችሉት የአገራቱ መሪዎች በሚወስዷቸው የፖለቲካ ውሳኔዎች መሆኑን ይናገራሉ።
የህግ ባለሙያው አቶ ፋሲል ስለሺ እንደሚሉትም በግብዕ ህገ መንግስት የአገሪቱ መሪ የአባይን ውሃ ታሪካዊ ባለቤትነትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ግዴታ ሆኖ ተቀምጧል።

በመሆኑም ስልጣን ላይ ያለው መሪ ይህን ለማመፈጸም የሌሎች የተፋሰሱ አገራትን መብትና ጥቅም ማክበር አዳጋች እንደሚሆንብት ይናገራሉ።
በተለይ ግብጽ የአባይን ውሃ አጠቃቀም በተመለከተ የሚደረጉ ስምምነቶችን የመቀበል ዝንባሌ የላትም ነው የሚሉት።
ከታችኞቹ ተፋሰስ አገሮች ጋር እኤአ ከ2012 ጀምሮ የተለያዩ ድርድሮች እየተደረጉ መሆኑን ያስታወሱት መሁራኑ ከአገራቱ ጋር የጋራ መግባባት እስኪፈጠር የሶስትዮሽ ድርድሩ መቀጠል እንዳለበት ያምናሉ።
ይሁንና ሶስቱ አገራት በድርድሩ ሂደት ሶስተኛ ወገን እንዲገባ ማድረግ ካለባቸው እንኳን ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትኤ ይሰጣሉ ተብለው በተቋቋሙ አህጉራዊ ድርጅቶች ሊሆን ይገባል ብለዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አሁናዊ ክንውኑ 73 በመቶ የደረሰ ሲሆን በመጪው ክረምት ውሃ መያዝ እንደሚጀምር ይጠበቃል።