የትግራይ ዓለም አቀፍ ስታዲየም አምስተኛ ምዕራፍ ግንባታ እየተካሄደ ነው

60

መቀሌ፤  ግንቦት 08/2012 ( ኢዜአ) የትግራይ ዓለም አቀፍ ስታዲየም አምስተኛ ምዕራፍ ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው ህዝባዊ መሰረት ያለው የስፖርት እድገት ዳይሬክተር ወይዘሮ ካህሱ ዜናዊ ለኢዜአ እንደገለጹት የስታዲየሙ ግንባታ አንድ ቢሊዮን 400 ሚሊዮን ወጪ ይጠይቃል።

ግንባታውን በመንግስት በጀት ብቻ ማካሄድ የማይቻል በመሆኑ ባለሃብቶችና የክልሉ ህዝብ ድጋፍ እንዲያደርጉ ዳይሬክተሯዋ ጠይቀዋል።

የባለሃብቶችና ህዝቡን ድጋፍ ታሳቢ በማድረግ የክልሉ መንግስት በመደበው 114 ሚሊዮን ብር በጀት  የስታዲዮሙ አምስተኛ ምዕራፍ ግንባታ ከሁለት ወራት በፊት መጀመሩንም  ገልጸዋል።  

"የስታዲየሙን ግንባታ በመካሄድ ላይ ያለው በተክለብርሃን አምባዬ ህንጻ ተቋራጭ ድርጅት ነው "ብለዋልወይዘሮ ካህሱ።

የስታዲየሙን  አምስተኛ ምእራፍ ግንባታ በ2014 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ለማጠናቀቅ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ያመለከቱት ሃላፊው፤ ከግንባታውም መካከል መታጠቢያ ክፍሎች፣ የቀሩ የአጥር ስራ የማሟላት፣የተመልካች ወንበሮች፣ የመብራትና ካሜራዎች የመገጣጠም ስራዎች ይገኙበታል።

ስታዲዮሙ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ሲበቃ በአንድ ጊዜ እስከ 50 ሺህ ተመልካቾች የማስተናገድ አቅም እንደሚኖረውም ተገልጿል።

የተቋራጭ ድርጅቱ መሃንዲስ ኢንጅነር ገብረመስቀል ህሉፍ እንዳሉት በገቡት ውል መሰረት ግንባታውን አጠናቀው ለማስረከብ ዝግጁ ናቸው።

በ1997 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው የትግራይ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከአንደኛ እስከ አራተኛ ምዕራፍ  ስራው የክልሉ መንግስት  ከ726 ሚሊዮን ብር በላይ  ወጪ ማድረጉም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም