ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ በችግር ምክንያት ምርጫ ሳይደረግ ሲቀር ክፍተቱን የሚሞላው የሕገ መንግሥት ትርጉም ነው -ምሁራን

አዲስ አበባ ግንቦት 8/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በችግር ምክንያት ምርጫ ሳይደረግ ሲቀር የአስፈጻሚ አካል ሥልጣንን በቀጥታ የሚመልስ ድንጋጌ ባለመኖሩ ክፍተቱን ለመሙላት የሕገ መንግሥት ትርጉም ዋነኛ አማራጭ መሆኑን ምሁራን ገለጹ፡፡

የኢፌዴሪ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ በሕገ መንግሥት ትርጉም ላይ ያዘጋጀው መድረክ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ በመሳተፍ ላይ የሚገኙት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህር ዶክተር ጌታቸው አሰፋና የአፍሪካ ሰብዓዊና ሕዝብ መብቶች ኮሚሽን ሊቀመንበር ዶክተር ሰለሞን አየለ በሰጡት አስተያየት አገሪቱ ባለችበት ሁኔታ   ሕገ መንግሥት  መተርጎም  ''አስፈላጊና የተሻለ አማራጭ'' ነው ይላሉ።

በሕገ መንግሥት ውስጥ የአስፈጻሚ አካል የምርጫ ዘመን ሲጠናቀቅ ምርጫ መደረግ  እንዳለበት እንጂ፤ በችግር ምክንያት ምርጫ ሳይደረግ ሲቀር ምን መሆን እንዳለበት  በቀጥታ የሚመልስ ድንጋጌ የለም ብለዋል፡፡

ከዚህም በተነሣም የሕገ መንግሥት ክፍተት ወይም ሕገ መንግሥቱ  እንዳልሸፈነው   ጠቁመዋል፡፡

ይህን ተከትሎ አሁን በአገሪቱ ላይ የመጣው ወረርሽኝ አደጋ ምርጫን ለማራዘም ምክንያት መሆኑንና  ለሕዝቡ ደህንነት ሲባል ምርጫው መራዘሙ ትክክል  መሆኑን ዶክተር  ጌታቸው አስረድተዋል፡፡  

በችግር ምክንያት የምርጫ መራዘም ሁኔታ አይቀሬ ሲሆን የአስፈጻሚ አካላት የስልጣን  ዘመን ምን መሆን እንደሚገባው ሕገ መንግሥቱ ስለማይመልስ በሕገ መንግሥት  ትርጉም ሊሸፈን ይችላል ብሎ ምክር ቤቱ መጠየቁ ተገቢ ጥያቄ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህም የሆነበት ምክንያት ሕገ መንግሥቱ በሰዎች ስለሚረቀቅና የሰው ልጆችም ማየት  እስከሚችሉበት ብቻ አይተው ሕገ መንግስቱን በማርቀቃቸው ምክንያት በሕገ መንግስቱ ውስጥ ክፍተት ተፈጥሯል ብለዋል፡፡

ክፍተቱ ሕገ መንግሥትን በማሻሻል፣ በሕገ መንግሥት ትርጉም ወይም ደግሞ አዎንታዊ የሆነ የሕገ መንግሥት ትግበራ /positiveconstitutionalpractice/ ሊሞላ እንደሚችል  ምሁሩ  አመልክተዋል፡፡

በሕገ መንግሥት ውስጥ ተዛማጅ ነገሮች ተነስተው ነገር ግን ተዛማጅ ነገሮች ተግባራዊ  ጥያቄ በቀጥታ የማይመልሱ ከሆነ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ  ማድረግ  ይገባል ብለዋል፡፡

አገሪቱ የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈለገው የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ላይ በመሆኗ  ያለውን የሕግ ክፍተት ይሞላል ተብሎ በመታሰቡ ነው ብለዋል፡፡

“ በአሜሪካ ሕገ መንግሥት በማህበር የመደራጀት መብት በግልጽ አልተመለከተም። ነገር  ግን ከሌሎች ተዛማች ህጎች ጋር በማቀናጀት  እንዲተገበር  ተደርጓል ”  ሲሉም  በአብነት አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ምርጫ በአምስት ዓመት መካሄድ እንዳለበት ይደነግጋል  እንጂ፣ በችግር ጊዜ መውጫው ምን እንደሆነ አልሸፈነም  በማለትም  ዶክተር ጌታቸው  አስረድተዋል፡፡  

ስለዚህም ተዛማጅ ከሆኑት የሕገ መንግሥት ድንጋጌ በትርጉም ክፍተቱ ሊሞላ ይችላል 

ሲሉም ጠቁመዋል፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54/1/ እና 58/3/ ምርጫ ዘመኑ ከማለቁ አንድ ወር በፊት መደረግ አለበት ተብሎ የተደነገገው ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ታይቶ ሊተረጎም እንደሚችል የተናገሩት ደግሞ የአፍሪካ ሰብዓዊና ሕዝብ መብቶች ኮሚሽን ሊቀመንበር ዶክተር ሰለሞን አየለ ናቸው።

ይህ ግልጽ የሆነ የሕገ መንግሥት ድንጋጌ በመሆኑ ትርጉም አያስፈልገውም የሚሉ አካላት ድንጋጌውን ከነባራዊ ሁኔታ አንጻር  ማየት  ይገባቸዋል፡፡

ሕገ መንግሥትም መተርጎም ያለበት አንቀጾች ለብቻ ተነጥለው ሳይሆን፤ ሕገ መንግስቱ አንድ ዓላማ እንዳለው የህገ ሰነድና እያንዳንዱ አንቀጽ ከሌሎች አንቀጾች ጋር ተናቦ የተፈለገውን ዓላማ እንዲሰጥ ተደርጎ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡  

ስለዚህም የአንቀጽ 54/1/ እና 58/3/ ትርጉም ከአንቀጽ 93 ጋር እና ከሌሎች ተገቢ ተዛማጅ ድንጋጌዎች ጋር አንድ ላይ ቢታዩ በተቃራኒ ጎራ የሚያነሱት ድምዳሜ ላይ መድረስ አይቻልም ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ስራ ላይ ባለበት ጊዜ መንግሥት በሥራ ላይ ሆኖ  ስላለባቸው የሕገ መንግስት ትርጉም መጠየቁ ተገቢ  መሆኑን ዶክተር ሰለሞን ገልጸዋል፡፡  

የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጁ እስካለ ድረስም የመንግሥት የሥራ ዘመን ሰለማያበቃ ሕገ መንግሥት ትርጉም መተርጎም አለበት ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም