በምርጫ ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ ሕገ መንግሥቱ ያስቀመጠው ነገር ስለሌለ መፍትሔው የሕገ መንግሥት ትርጉም ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምርጫ ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ ሕገ መንግሥቱ ያስቀመጠው ነገር ስለሌለ መፍትሔው የሕገ መንግሥት ትርጉም ነው
የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ምርጫ በሚደረግበት ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ ምን መደረግ እንዳለበት በግልጽ ስላላስቀመጠ መፍትሔው የሕገ መንግሥት ትርጉም መሆኑን ምሁራን ገለጹ።
አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ እንዲታወጅ ያስገደደውን ጉዳይ ለመከላከል ቅድሚያ መስጠት ሕገ መንግሥታዊ መርህ መሆኑም ተገልጿል።
የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለቀረበለት የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የባለሙያዎችን አስተያየት በማሰባሰብ ላይ ይገኛል።
ጉባዔው ምርጫ በሚደረግበት ወቅት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 ቁጥር 1 መሠረት ከአቅም በላይ የሆነ አደጋ፣ የውጭ ወረራ፣ ሕገ መንግሥቱን አደጋ ላይ የሚጥል ችግር፤ በሽታ ወይም ወረርሽኝ ሲከሰት ምን መደረግ አለበት? ሌሎች ሀገራት በሕገ መንግሥታቸው መሠረት የሚወስዱት አማራጭስ ምንድን ነው? የሚል ጥያቄ ለምሁራን ቀርቧል።
ምሁራኑም የቀረበላቸውን ጥያቄ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ከዓለም አቀፍ ተመክሮ ጋር አዛምደው ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የአፍሪካ የሰብዓዊና ሕዝብ መብቶች ኮሚሽን ሊቀ መንበር ዶክተር ሰለሞን አየለ እንዳሉት፤ የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ምርጫ በሚደረግበት ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚያሳውጅ አደጋ ሲከሰት "ምን ይደረግ" ለሚለው ግልጽ ድንጋጌ አላስቀመጠም።
የፖላንድ ሕገ መንግሥት አዋጅ በታወጀ በ90 ቀናት ውስጥ ማካሄድ እንደማይቻል፤ የሕንድና ሞሪሽየስ ሕገ መንግሥት ደግሞ በስድስት ወር ውስጥ ምርጫ መካሄድ እንዳለበት በግልጽ መደንገጋቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ግን ምርጫና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በተመለከተ "እንዴት፣ መቼ፣ ምን" ይደረግ የሚለውን በግልጽ አላስቀመጠም ነው ያሉት።
በዚህም በኢትዮጵያ በተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የታወጀው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅና ምርጫን በተመለከተ የተለያዩ የሕግ ባለሙያዎች የተለያዩ ሀሳብ ይሰጣሉ ብለዋል።
ይሁን እንጂ ሁሉም የሕግ ባለሙያዎች ባላቸው የቴክኒክ ዕውቀት ልክ አስተያየት ቢሰነዝሩም የመጨረሻውን ውሳኔ የሚያሳልፈው ሕገ መንግሥት የመተርጎም ሥልጣን የተሰጠው አካል መሆኑን ገልጸዋል።
የሕገ መንግሥት ማሻሻያ በማድረግ መፍትሔ መስጠት የሚያስችል ነባራዊ ሁኔታ የለም፤ ሁልጊዜ ችግር ሲፈጠር ሕገ መንግሥት ይሻሻል ከተባለም ተርጓሚውን አካል አላስፈላጊ ያደርገዋል ብለዋል።
በመሆኑም በኢትዮጵያ የተከሰተው ወቅታዊ ችግር መፍትሔ የሚያገኘው ሥልጣን በተሰጠው አካል የሕገ መንግሥት ትርጉም ሲሰጥበት መሆኑን አብራርተዋል።
የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮችን የማጣራት ሥልጣን በሕገ መንግሥቱ ተሰጥቶታል።
በሚያደርገው ማጣራትም ሕገ መንግሥቱን መተረጎም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ የውሳኔ ሀሳብ ያቀርባል።
በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 83 ቁጥር 2 መሠረትም የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ በሚያቀርብለት ሕገ መንግሥታዊ ጉዳይ ላይ በ30 ቀናት ውስጥ ውሳኔ ይሰጣል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህር ዶክተር ጌታቸው አሰፋ፤ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ እንዲታወጅ ያደረገውን ነገር ለመከላከል ቅድሚያ መስጠት ሕገ መንግሥታዊ መርህ እንደሆነ ይገልጻሉ።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የተወሰኑ መብቶች የመናገር መብትን ጨምሮ ሰላማዊ ሰልፍ፤ ስብሰባ ማድረግ በጊዚያዊነት እንደሚገደቡ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ምርጫው እንዲራዘም መደረጉም የዚሁ ሕገ መንግሥታዊ መርህ አንዱ አካል ተደርጉ ይወሰዳል ነው ያሉት።
በዓለም ላይ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት 47 ምርጫዎች መራዘማቸውን የገለጹት ዶክተር ጌታቸው፤ ቦሊቪያ ብሔራዊ ምርጫ፤ ኬኒያ፣ ብራዚል፣ ካናዳ፣ ጀርመን ክልላዊ ምርጫ እንዲሁም ቺሊ፣ ሩሲያ ሕዝበ ወሳኔዎች እንዲራዘሙ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።