ቀጥታ፡

የህገ መንግስት ትርጉምን በሚመለከት የባለሙያዎች መድረክ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ ግንቦት 8/2012( (ኢዜአ) ) የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የህገ መንግስት ትርጉምን በተመለከተ ያዘጋጀው የባለሙያዎች ሀሳብ መስጫ መድረክ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ነው። 

ዘንድሮ ይካሄዳል ተብሎ ቀን ተቆርጦለት የነበረው ስድስተኛ ብሄራዊ ምርጫ በኮቪድ 19 ምክንያት ማካሄድ ስለማይቻል እንዲራዘም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረቡ የሚታወስ ነው።

ምክር ቤቱም ከህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበለትን የመፍትሄ ሃሳብ በማፅደቅ ለህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ መላኩ ይታወሳል፡፡

በመሆኑም የህገ መንግስት ትርጓሜ  ለመስጠት ጉዳዩ የሚመለከታቸው የህግና ምርምር ተቋማት፣ የህግ መንግስት ባለሙያዎች፣ ህገ መንግስት በማርቀቅ አስተዋጽኦ የነበራቸው ባለሙያዎችና የህግ ባለሙያዎች የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።

የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ሰብሳቢና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ማአዛ አሸናፊ ውይይቱ ህገ መንግታዊ ጥያቄዎች የጠራ ትርጉም እንዲያገኙ ጥሩ አጋጣሚ የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

የህግ መንግስት ትርጉም የአተረጓጎም ጥበብን ከማሳደግ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ህግ መንግስታዊ ስርዓት እንዲሰርጽ ልዩ አጋጣሚን የሚፈጥር መሆኑንም አብራርተዋል።

የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንትና ምክትል ፕሬዘዳንት በሰብሳቢነትና ምክትል ሰብሳቢነት፤ ስድስት የሕግ ባለሙያዎችና ሶስት ከፌደሬሽን ምክር ቤት የተወከሉ በድምሩ 11 አባላት አሉት።

አጣሪ ጉባኤው ህገ መንግስታዊ ጉዳዮችን የማጣራት ስልጣን ተሰጥቶታል።

በሚያደርገው ማጣራትም ህገ መንግስቱ መተረጎም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ የውሳኔ ሃስብ የሚያቀርብ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም