ኮርፖሬሽኑ ለድርጅቶችና መኖሪያ ቤት ተከራዮቹ በድጋሚ የ50 በመቶ የአንድ ወር የኪራይ ቅናሽ አደረገ

100

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 7/2012  ዓ.ም ( ኢዜአ) የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ለ18 ሺህ 153 ድርጅቶችና መኖሪያ ቤት ተከራዮች በድጋሚ የ50 በመቶ የግንቦት ወር ቅናሽ ማድረጉን አስታወቀ።

ኮርፖሬሽኑ ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን ለመከላከል ያበረከተው አስተዋጽኦ 130 ሚሊዮን ብር ደርሷል ።

ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው በአዲስ አበባና ድሬዳዋ ለሚገኙ ለድርጅቶችና የመኖሪያ ቤት ተከራዮች ኮቪድ-19 የፈጠረባቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቀነስ ቀደም ሲል የሚያዚያ ወር ቅናሽ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

የመንግስት አቅጣጫን በመከተል ኮርፖሬሽኑ በየወሩ እየተከታተለ ቅናሽ ለማድረግ ቀደም ብሎ በገባው ቃል መሰረት የግንቦት ወር 50 በመቶ የኪራይ ዋጋ ቅናሽ ለተከራዮቹ አድርጓል።

ኮርፖሬሽኑ ባደረገው የ50 በመቶ ወርሃዊ የኪራይ ክፍያ ቅናሽ 11 ሺህ 860 የመኖሪያና 6 ሺህ 293 ድርጅቶችን በቀጥታ ተጠቃሚ ያደርጋል።

ከእነዚህም ውስጥ  ወርክሾፖች፣ ሱቆች፣ መጋዘኖች፣ አዳራሾች፣ ሆቴሎችና ሌሎችም ይገኙበታል።

በዚህም ኮርፖሬሽኑ በሚያዚያና ግንቦትና ወር ለመሰበስበው ካቀደው 240 ሚሊዮን ግማሹን ለተቋሙ ደንበኞች የቤት ኪራይ ዋጋ ቅናሽ አድርጓል።

በተጨማሪም ለኮቪድ-19 መከላከል ድጋፍ አሰባሳቢ ብሔራዊ ኮሚቴ 10 ሚሊዮን ብር በማርከት እስካሁን በሽታውን ለመከላከል የ130 ሚሊዮን ብር ድጋፍ  ማበርከቱን ገልጿል።

ኮርፖሬሽኑ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል እያደረገ ያለው ርብርብ፣ በበጀት ዓመቱ ያቀዳቸው ስራዎች ላይ  ከፍተኛ ተጽእኖ እንዳይፈጥር ከወዲሁ እየሰራ መሆኑን ገልጿል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም