ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በቡና ምርት ላይ የወሰደችው የአሰራር ማሻሻያ የውጭ ምንዛሬዋን እንዲያድግ አሳድጓል

አዲስ አበባ ግንቦት 7/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በቡና ምርት ላይ የተዘረጋው አዲስ አሰራር አገሪቱ በቡና ምርት የምታገኘውን የውጭ ምንዛሬ እንዲያድግ ከማድረጉም ባለፈ በዘርፉ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ተጠቃሚነት እንደጨመረ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ በቡና ምርት ላይ የወሰደውን አዲስ የአሰራር ማሻሻያና ግኝት በተመለከተ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል።

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ኡመር በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የተዘጋጀው መመሪያ የተዋናዮቹን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፣ አገሪቱ የተሻለ ገቢ እንድታገኝ ለማድረግና የገዥዎችን ፍላጎት ለሟሟላት የሚያስችል ነው።

በዚህም ባለፈው ወር ብቻ 97 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወደ ውጭ ከሚላከው የቡና ምርት ገቢ ለማግኘት ታስቦ 104 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ተገኝቷል።

''አርሶ አደሩም በተዘረጋለት አሰራር ከአምራችነት ከሚያገኘው ገቢ እስከ ምርቱን ውጭ ገበያ የማቅረብ ስልጣን ይሰጠዋል'' ብለዋል።

በዚህም እስካሁን ቡና አምርተው ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ፍላጎት ያላቸው 600 የሚሆኑ አርሶ አደሮች  የተመዘገቡ ሲሆን 60 የሚሆኑ  ምርታቸውን ወደ ውጭ መላክ ጀምረዋል።

በዚህም ህገ-ወጥ ደላሎች የሚያሳድሩትን ጫና ማቃለል እንደተቻለ ጠቁመዋል።

አሁን የተዘረጋው አሰራር ይህንን በዘርፉ ያለውን ችግር በማቃለል አገሪቱ በዘርፉ የተሻለ የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝና በዓለም ገበያ የመደራደር አቅሟን እንደሚያሳድግ ገልጸዋል።

የአቅራቢና የላኪ የግብይት አማራጮች ማስፋት፣ የልዩ መስኮት የገበያ ትስስር መፍጠር፣ የመኪና ላይ ሽያጭና የቅሬታ አፈታት ላይ አዳዲስ የማሻሻያ መመሪያዎች ወጥተዋል።

ለአገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ፣ ለላኪዎች ማቅረብ እንዲሁም ወደ ውጭ በቀጥታ በመላክ ለደላሎች ብቻ ማቅረብ ላይ ተወስኖ የነበረውን የገበያ አማራጭ ማስፋት መቻሉን ገልጸዋል።

የቡና ጥራትን በመጨመር ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የቡና ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ አድርጓል።

በዚሀም አገሪቱ ለበርካታ ዓመታት አጥታው የነበረው የቡና ገቢ እድገት ማምጣት እንደተቻለ ጠቁመዋል።

የኮሮና ቫይረስ በቡና ምርት ላይ ጠንከር ያለ ተጽዕኖ እንዳላሳደረ የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ የቡና ገበያ ፍላጎት መጨመሩን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም