ቀጥታ፡

ባለሀብቱ ለ370 ችግረኞች የምግብ እህል ድጋፍ አደረጉ

ሐረር ግንቦት 7/2012 ( ኢዜአ) የሐረር ከተማ ተወላጅ የሆኑት ባለሀብት በአካባቢው ኮሮና ባስከተለው ተጽዕኖ ለተገሩ 370 አቅመ ደካሞች እና አካል ጉዳተኞች የምግብ እህል ድጋፍ አደረጉ። 

ባለሀብቱ አቶ ጸጋዬ አበበ  ድጋፉን ባበረከቱበት ወቅት እንደተናገሩት ያደረጉት ድጋፍ 680ሺህ  ብር በሆነ ወጪ የተለያዩ የምግብ ዓይነቶች በመግዛት ነው።

እነዚህም ማካሮኒ ፣ ፓስታ፣ዱቄት እና የምግብ ዘይት መሆኑን አመልክተው በቅርቡ በከተማው በተከሰተው ድንገተኛ ጎርፍ  13 ከብቶቻቸው ለሞቱባቸው አንድ ግለሰብ ደግሞ የ50 ሺ ብር ድጋፍ ማድረጋቸውንም አውስተዋል።

የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እና የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ሰብሳቢ አቶ ኦርዲን በድሪ  የአካባቢው ተወላጅ የሆኑት ባለሀብቱ  ላደረጉት ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ድጋፉን ያገኙት ወገኖች ምግብ ፍለጋ ከቦታ ቦታ ሳይንቀሳቀሱ በቤት እንዲቆዩ ለማስቻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸው ሌሎች ባለሀብቶችም እገዛቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ለእነዚህ ወገኖች የተደረገው ድጋፍ ለአንድ ወር ቀለብ እንደሚሆናቸው ተናገሩት ደግሞ የክልሉ የገቢ አሰባሰብና ፈንድ አገፈላላጊ ሰብሳቢ ወይዘሮ አሚና አብዱከሪም ናቸው።

የድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል በከተማው የሐማሬሳ  አካባቢ ነዋሪ  ወይዘሮ በቀለች ዲልጋሳ በሰጡት አስተያየት ያገኙት  ድጋፍ ችግራቸውን ለማቃለል እንደሚረዳቸው ገልጸዋል።

አቶ ማሙሽ አንበሴ በበኩላቸው  ድጋፉ  እሳቸውና ቤተሰባቸው ያጋጠማቸውን ወቅታዊ ችግር ለመቋቋም እንደሚያግዛቸው  በማመልከት ለዚህም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ድጋፉን የሰጡት ባለሀብት   በምስራቅ ሸዋ ቆቃ እና ሰበታ አከባቢ  የውጭ  ምንዛሬ በሚያስገኝ የአበባና ፍራፍሬ ልማት ላይ የተሰማሩ እንደሆኑ  ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም