ቀጥታ፡

በደቡብ ክልል ከኮቪድ-19 መከላከል በተጓዳኝ የሌሎች በሽታዎች የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 7/2012  ዓ.ም ( ኢዜአ) በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን ከመከላከል በተጓዳኝ የሌሎች በሽታዎችን መድሃኒት አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ መድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ አስታወቀ።

በኤጀንሲው የደቡብ ክላስተር አስተባበባሪ አቶ ዘመን ለገሠ ኤጀንሲው ከዚህ ቀደም ቅሬታ ይነሳበት የነበረውን የአገልግሎት አሰጣጥ ካይዘን የለውጥ መሳሪያዎችን በመተግበሩ ማሻሻሉን ተናግረዋል።

ከግዢ ጀምሮ የተለያዩ የለውጥ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።

የጤና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም የመድሃኒት ፍላጎት ጥያቄ የማቅረብ ሂደታቸውን ማሻሻላቸውን ተናግረዋል።  

ኤጀንሲው በነጻና በሽያጭ የሚከፋፈሉ መድኃኒቶችን እንደሚያሰራጭ ገልጸው ፤ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከገባ ጀምሮ ለመከላከያ የሚሆኑ የህክምና ግብዓቶችን በመጋዘን ውስጥ ሳይቆዩ በፍጥነት እያከፋፈለ መሆኑን ገልጸዋል።

በአቅርቦትና ፍላጎት መካከል አለመጣጣም ቢኖርም ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያስችሉ ግብዓቶች በሁሉም የጤና ተቋማት እየተሰራጩ እንደሆነም አስረድተዋል።

ማስተባበሪያው ሰራተኞቹንና ደንበኞቹን ከኮቪድ-19 ተጋላጭነት ለመጠበቅ የሚውል ሳኒታይዘር አምርቶ እየተጠቀመ እንደሆነም ገልጸዋል።

የወቅቱ ትኩረት የኮሮና ቫይረስ ቢሆንም በደቡብ ክልል ሌሎች እንደ ኮሌራና ወባ መሰል ተጓዳኝ በሽታዎች ጉዳት እያደረሱ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በነጻ ከሚሰራጩ እንደ ቲቢ፣ ኤች አይቪ እና  ሌሎች የፕሮግራም ክትባቶች በተጨማሪ ለተጓዳኝ በሽታዎች መከላከያ መድኃኒቶችን ለጤና ተቋማት ለማዳረስ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

በዋና መሥሪያ ቤቱ በኩልም ከውጭ ግዥ የተፈጸመላቸው የመድኃኒትና ሌሎች የህክምና ግብዓቶች እንዳሉ ጠቅሰው፤ አቅርቦቱም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የተናገሩት።

ሌሎች ወረርሽኞች የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቀነስም ኤጀንሲው ብቻ ሳይሆን ሌሎች የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለት ባለድርሻ አካላትም ርብርብ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም