የግብርና ሴክተርን ለማዘመን በሰብል፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት እየተከናወነ ያለው ተግባር ተስፋ ሰጪ ነው ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
የግብርና ሴክተርን ለማዘመን በሰብል፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት እየተከናወነ ያለው ተግባር ተስፋ ሰጪ ነው ተባለ
አዳማ ኢዜአ/ ግንቦት 07/2012 በኦሮሚያ ክልል የግብርና ሴክተርን ለማዘመን በሰብል፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት እየተከናወነ ያለው ተግባር ተስፋ ሰጪ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስቴሩ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ ኮሚቴዎች ገለጹ።
በፌዴራል መንግስት የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ ኮሚቴዎችና በክልሉ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች የተመራው የግብርና ልማት ስራዎች ጉብኝት በምስራቅ ሸዋ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች እየተካሔደ ነው።
የጉብኝቱ ተሳታፊዎች እንደሚሉት ታዲያ በኦሮሚያ ክልል የግብርና ሴክተርን ለማዘመን በሰብል፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እየተከናወነ ያለው ተግባር አገሪቷ ከውጭ የምታስገባቸው ምርቶች ለመተካትና በምግብ ሰብል ራስን ለመቻል ተስፋ ሰጪ ነው።
የጠቅላይ ሚኒስቴሩ ሲኒየር የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ እንደገለጹት ሀገሪቷ ስንዴን ከውጭ ለማስገባት በየዓመቱ ከ500 እስከ 700 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ታወጣለች።
ከውጭ የሚገባውን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት የውጭ ምንዛሪ ለማዳን በኦሮሚያ ክልል በሰብል፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት እየተከናወነ ያለው ተግባር የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።
በአንድ የአርሶ አደር ማሳ ላይ በዓመት ሶስት የተለያየ ሰብል ማምረት እንደሚቻል "በተግባር እያየን ነው" ያሉት አቶ ተክለወልድ ይህም ለሌሎች አካባቢዎች ጭምር አስተማሪና ተሞክሮ የሚወሰድበት ነው ብለዋል።
ለቀጣዩ ሁለት ዓመት የአቮካዶ ልማትን ጨምሮ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ሰፋ አድርገን ከሄድንበት አሁን ሀገሪቷ ከጠቅላላው ግብርና ምርት የምታገኘውን 3 ቢሊዮን ዶላር በአቮካዶ ልማት ብቻ ማግኘት እንችላለንም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ በበኩላቸው በኮሮና ቫይረስ የግብርና ሴክተር እንዳይጎዳ የዘርፉን ልማትና ምርታማነት በተጠናከረ ሁኔታ ለማካሄድ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በጉብኝቱ ደግሞ "በኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የሆነ የግብርና ልማት እንቅስቃሴ ተመልክተናል" ያሉት ዶክተር ይናገር በተለይም የስንዴ መስኖ ልማት እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬ በጥሩ ሁኔታ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የክልሉ መንግስት አርሶ አደሮቹን በቴክኖሎጂ፣ በግብዓት አቅርቦትና በገበያ ትስስር እየደገፈ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ይናገር የግብርናውን ሴክተር በፋይናንስ ለመደገፍ በትኩረት እየሰራን ነው ብለዋል።
ከዚህ በፊት አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ተንቀሳቃሽ ሀብታቸውን አስይዘው መበደር አይችሉም ነበር ያሉት ዶክተር ይናገር አሁን ግን ተንቀሳቃሽ ሀብቱን በማስያዝ መበደር እንዲችል መንግስት የተንቀሳቀሽ ሀብት አዋጅ በማፅደቅ ወደ ተግባር መግባቱን ገልጸዋል።
በተጨማሪም በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የሀገሪቷ ክፍለ ኢኮኖሚ እንዳይጎዳና ፈጥኖ ማገገም እንዲችል ለንግድ ባንክ 16 ቢሊዮን፣ ለግል ባንኮች ድጎማ 15 ቢሊዮን፣ ለማክሮ ፋይናንስና ትሬዠሪ ቢል 17 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ሀብት መመደቡን ተናግረዋል ።
በኦሮሚያ ክልል በግብርና ሴክተር እየተካሄደ ያለው ልማት የአርሶ አደሩን ህይወት በዘላቂነት የሚለውጥ ጥበብ ነው ያሉት ደግሞ የኮሚቴው አባል አምባሳደር ግርማ ብሩ ናቸው።
በተለይም በውሃ አጠቃቀም፣ የግብዓት አቅርቦት፣ የብድር አገልግሎትና የገበያ ትስስር ክፍተት ከአርሶ አደሩ የሚነሳ ቅሬታ በመሆኑ ይህን ችግር ለመቅረፍ እንደሚሰራ ጠቁመዋል ።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እንደገለጹት የአርሶ አደሩንና የአርብቶ አደሩን ህይወት በዘላቂነት ለመለወጥ ለመካናይዜሽን ግብርና 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ብድር መቅረቡን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በቡና ልማትና ኤክስፖርት ለተሰማሩ የህብረት ሥራ ዩኒየኖች ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ የብድር አገልግሎት አመቻችተናል ብለዋል።
ለ2012/2013 ዓ.ም የምርት ዘመን በኮሮና ቫይረስ ምንክንያት የእጅ በእጅ ሽያጭን ለጊዜው በመግታት አርሶ አደሩ 20 በመቶ በመክፈል ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በብድር እንዲያገኝ ሁኔታዎችን መመቻቸታቸውንም ፕሬዝዳንቱ ገልፀዋል ።