በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለተቸገሩ አንድ ሺህ 850 አቅመ ደካሞች ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለተቸገሩ አንድ ሺህ 850 አቅመ ደካሞች ድጋፍ ተደረገ
ደሴ/ፍቼ/ ግንቦት 7/2012 (ኢዜአ) ቀለም ኢትዮዮጵያ የተባለ በጎ አድራጎት ማህበር እና ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለተቸገሩ አንድ ሺህ 850 አቅመ ደካሞች የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ።
በማህበሩ የኮምቦልቻ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኑሩ መሃመድ እንደገለጹት አንድ ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ 200 ኩንታል የምግብ እህል ገዝተው በደቡብ ወሎ፣ ኦሮሞ ብሔረሰብና ሰሜን ወሎ ዞኖች ለሚገኙ 1ሺህ 300 አቅመ ደካሞች ድጋፍ አድርገዋል።
ማህበሩ የቫይረሱን ስርጭትን መቆጣጠር እስከሚቻል ድረስ ከመንግስት ጎን በመቆም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አቶ ኑሩ አስታውቀዋል።
በደቡብ ወሎ ኮምቦልቻ ከተማ ማህበሩ ዛሬ ድጋፍ ባደረገበት ወቅት የተገኙት የከተማው አስተዳደር የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ምክትል ሰብሳቢ አቶ አህመድ የሱፍ "ይህን አስቸጋሪ ወቅት ማለፍ የምንችለው ሁሉም አካላት የጋራ ርብርብ በማድረግ ነው" ብለዋል።
እስካሁንም ባለሃብቱ፣ ነጋዴውና በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ለሁለት ሺህ 500 በላይ ለሚሆኑ አቅመ ደካሞች ድጋፍ ማድረጋቸውን አውስተው ዛሬ በኮምቦልቻ ከተማ ለሚኖሩ 200 አቅመ ደካሞች በማህበሩ ድጋፍ መሰጠቱን ገልጸዋል።
በኮምቦልቻ ከተማ የቀበሌ አንድ ነዋሪ ወይዘሮ ፋጡማ ሰይድ በሰጡት አስተያየት "ወቅቱ ረመዳን ቢሆንም ሦስት ቤተሰብ ይዤ ባዶ ቤት በመቀመጤ ለጭንቀት ተዳርጌ ነበር" ብለዋል።
አሁን በማህበሩ የተደረገላቸው 15 ኪሎ ግራም ዱቄትና ሩዝ ጊዜያዊ ችግራቸውን እንደሚያቃልልላቸው በመግለጽ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ሌላው የ04 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ግርማ ይማም አቅመ ደካማ በመሆናቸው ትንሽ "ኮንቲነር" በወር 500 ብር አከራይተው ሶስት ቤተሰብ ያስተዳድሩ እንደነበር ጠቁመው ገበያ በመጥፋቱ ኪራዩ መቋረጡን ተናግረዋል።
ሰሞኑን ከበጎ አድራጊዎች ያገኙት የምግብ እህል ድጋፍ ችግራቸውን ለማቃለል እንደረዳቸው ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ በፍቼ ከተማ ኮሮናን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ለማገዝ ስድስት መቶ ሺህ ብር ግምት ያላቸው ቁሳቁሶች አበርክቷል።
የዩኒቨርሲቲው ኘሬዚዳንት ዶክተር ገናናው ጐፌ እንዳሉት ተቋሙ ዛሬ ያበረከታቸው ቁሳቁሶች ለ55ዐ አቅመ ደካማ ወገኖች ውርሃዊ ቀለብ የሚሆን የጤፍ ፣ የምግብ ዘይትና የንፅህና መጠበቂያ ናቸው።
ድጋፉ የተገኘው ከዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ሰራተኞችና መምህራን እንደሆነ አመልክተዋል።
ተቋሙ ቫይረሱን ለመከላከል የጤና ሳይንስ ፋክሊቲውን ሙሉ በሙሉ ለለይቶ ማቆያ እንዲውል ለዞኑ አስተዳደር ከማስረከቡም ሌላ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ዘጠና አባወራዎች የጤና መድህን ዋስትና አገልግሎት እንዲያገኙ ድጋፍ ማድረጉንም አውስተዋል።፡
ድጋፉ ሲሰጥ የተገኙት በኦሮሚያ የሰሜን ሸዋ ዞን ምክር ቤት ሰብሳቢና የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ኃይል አባል አቶ ጋሻው አክሊሉ ዩኒቨርሲቲው ኮሮናን ለመከላከል እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው ድጋፍ ካገኙት መካከል የፍቼ ከተማ ነዋሪው ጡረተኛ ኃይለማርያም አጥናፉ በተሰጣቸው የምግብ እና ንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ መደሰታቸውን ተናግረዋል ።