ለአርሶ አደሮች በ8028 ነጻ የስልክ መስመር መረጃዎችን እንደሚያደርስ የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ

113

አዲስ አበባ ግንቦት 7/2012 (ኢዜአ)በኢትዮጵያ ለሁሉም አርሶአደሮች በ8028 ነጻ የስልክ መስመር ከግብርና ጋር የተያያዙ መረጃዎችን እንደሚያደርስ የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ የአርሶ አደሩን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተጋላጭነት በመቀነስ ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎችን እንደሚያከናውንም ተገልጿል።

በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ለማ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የግብርና ኤክስቴንሽን ስራዎች ለውጥ እንዲያመጡ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው።

ከዚህ ቀደም ለአራት ሚሊዮን ለሚሆኑ አርሶ አደሮች ተደራሽ ይደረግ የነበረውን የነጻ የስልክ መስመር የግብርና መረጃ ለሁሉም አርሶ አደሮች እንዲደርስ ለማድረግ ዝግጅት ተደርጓል።

ለአርሶ አደሩ የሚደርሱ መረጃዎች በተለያዩ ቋንቋ የሚዘጋጁ መሆናቸውን ገልጸው፤ በጽሁፍና በድምጽ መልዕክቱ እንዲደርስ የሚደረግ መሆኑ ጠቁመዋል።

በነጻ የስልክ መስመር የሚደርሱ መልዕክቶች በተለያዩ መገናኛ ብዙሃንና በግብርና ባለሙያዎች በኩል በድጋሚ የሚተላለፉ እንደሚሆኑም አመልክተዋል።

በሌላ በኩል አርሶ አደሩ በመኸር ስራው ወቅት ለኮሮናቫይረስ ተጋላጭ እንዳይሆን የጥንቃቄ ርምጃ ለመውሰድ ዝግጅት መደረጉን የተናገሩት አቶ ኢሳያስ፤ ''የአርሶ አደር አካላዊ ርቀትን ለማስጠበቅ ከዚህ ቀደም የነበሩ የደቦና ጅጊ አሰራሮች አይኖሩም'' ብለዋል።

በመሆኑም አርሶ አደሩ የኮሮናቫይረስ ተጋላጭነቱን በመቀነስ በማሳው ላይ ውጤታማ እንዲሆን በትኩረት እንዲሰራ አስገንዝበዋል።

አርሶ አደሩ ግብዓት በአስቸኳይ እንዲደርሰው ለማስቻል እየተሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ ኢሳያስ፤ ዘንድሮ የማዳበሪያ ግዢ ቀደም ብሎ መፈጸሙን ተናግረዋል።

በመሆኑም የስርጭት መርሃ ግብር በማውጣት መተፋፈግ በማይፈጠርበት መንገድ የግብዓት ስርጭት እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።

በዘንድሮ የመኸር ወቅት በመደበኛ ፕሮግራም 12 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄከታር መሬት ለማልማት የታቀደ ሲሆን ከዚህም ከ335 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም