የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት በመቀናጀት አንድ ጠንካራ ተቋም እንዲፈጥሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ጥሪ አቀረቡ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት በመቀናጀት አንድ ጠንካራ ተቋም እንዲፈጥሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ጥሪ አቀረቡ
አዲስ አበባ ግንቦት 7/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት በመቀናጀት ከአገር አልፎ ለሌሎች አገሮች የሚተርፍ አንድ ጠንካራ ተቋም እንዲፈጥሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ጥሪ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን፣ ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እና ከኢትዮጵያ ወንጌላውያን ህብረት ካውንስል የእምነት መሪዎች ጋር ዛሬ ማለዳ ውይይትይ አካሂደዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውይይቱ መክፈቻ ላይ በአንዳንድ አገሮች መሰረታዊ የጋራ መርህ ያላቸው የሀይማኖት ተቋማት በጋራ ትላልቅ ስራዎችን እንደሚሰሩ አንስተዋል።
በኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት የጋራ መርህ ላይ ተመስርተው አንድ ጠንካራ ተቋም ቢመሰርቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ችግር ከመፍታት አልፈው ለሌሎችም መትረፍ እንደሚቻል ገልጸዋል።
በሺህ አመት የሚቆጠር ታሪክ ያላቸው የኢትዮጵያ ሀይማኖቶች የጋራ መርህ ላይ ተመስርተው አንድ ጠንካራ ተቋም በመፍጠር 96 በመቶ አማኝ የሆነውን ህዝብ በስራቸው ማሰለፍ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
ከዚህ ቀደም በሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሲሠራ የቆየውን ጠንካራ ስራ ከፍ በማድረግ ዘመን ተሻጋሪ ሥራ ለመሥራት የሀይማኖት ተቋማቱ በጋራ ሆነው እንዲሠሩ ምክረ ሀሳበ አቅርበዋል።
ከላይ የታሰበውን ትልም ታች ለማውረድ ሀይማኖቶች ያላቸው ተሰሚነት ከፍ ያለ በመሆኑ የጋራ ጠንካራ ተቋም በመፍጠር ትውልድ የሚያንጽና አገር የሚያበለጽግ ስራ መስራት እንደሚቻል ገልጸዋል።
ለአብነትም ድምጽ ለሌላቸው ችግረኞች ድምጽ በመሆን፣ በሰላም ግንባታ፣ በአደጋ ግዜ ዝግጁነት፣ የህዝቦችን ማህበራዊ ደህንነት በማረጋገጥ እና በበጎ ፈቃድ መሰል ስራዎች ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማበርከተ እንደሚችሉ ነው የገለፁት።
''ይህን በማድረግ ኢትዮጵያ መታገዝ ብቻ ሳይሆን ማገዝ የምትችል አገር መሆኗን በተግባር ስራ ማሳየት ይገባል'' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የተከማቸውን እውቀትና እሴት ለዚሁ በጎ ዓላማ ማዋል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ይህን እውን ለማድረግ ዝርዝር ሁኔታው በቀጣይ በጥናት እየታየ እንደሚመለስ እና ተቋማቱ ሰብሰብ ብለው አንድ ጠንካራ ተቋም በመፍጠር በሞራል ልዕልና እና ትውልድ ግንባታ አሻራቸውን እንዲያኖሩ ጠይቀዋል።
የኃይማኖት መሪዎቹ በበኩላቸው ይፈጠር በተባለው አዲስ ተቋም ያላቸውን አስተያየት እና ጥያቄ አንስተዋል።
በዚህም ጠንካራ ተቋም መመስረቱ ላይ በመስማማት ቀጣይ አደረጃጀት እና አሠራር ላይ ውይይት እንደሚያስፈልገው ነው ያነሱት።
ይሄንን ጠንካራ ተቋም እውን በማድረግ ብሄራዊ ገጽታን ለመቀየር እና በአገር ላይ በጎ ተጽዕኖ ለማሳረፍ እንደሚሠሩ ጭምር ነው የተናገሩት።