ቀጥታ፡

መንግስት ለፊልሞች እድገት ድጋፍ እንዲያደርግ የዘርፉ ባለሙያዎች ጠየቁ

አዲስ አበባ ሰኔ 28/2010 ፊልሞች የኢትዮጵያን ባሕልና እሴት የሚያንፀባርቁ እንዲሆኑ መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግ የፊልም ባለሙያዎች ጠየቁ። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባህል ማዕከል ከፊልም ሰሪዎች ማህበር ጋር በመተባበር ''በኢትዮጵያዊ ፊልሞች ውስጥ ኢትዮጵያዊነት አለ?'' በሚል ርዕስ  በአዲስ አበባ ውይይት እየተካሄደ ነው። በዘርፉ የመነሻ ጥናት ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር ኤፍሬም ለማ እንዳሉት ኢትዮጵያ በሌላው ዓለም ላይ የማይገኙ የተፈጥሮ፣ ባህልና የተለያዩ እሴቶች ባለቤት ነች፤ነገር ግን እነዚህ ሃብቶች ወደ ፊልም ቀይሮ በማስተዋወቅ ረገድ የተሰራው ስራ  ዝቅተኛ ነው። የኢትዮጵያን  የሙዚቃ  ቅኝት፣ የክር ምት፣ ዋሽንትና ማሲንቆን በፊልሞች ውስጥ አስገብቶ በማስተዋወቅ ረገድም ብዙ እንደሚቀር ነው  መምህር ኤፍሬም የተናገሩት። ''ፊልሞቻችን ኢትዮጵያ ውስጥና በኢትዮጵያውያን ስለተሰሩ ብቻ ኢትዮጵያዊነት ያንጸባርቃሉ ማለት እንዳልሆነም'' ነው መምሕር ኤፍሬም በጥናታቸው የገለጹት። ይህንን መነሻ አድርጎ አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ዳግም ታመነ  ''የኢትዮጵያ ፊልሞች 99 በመቶ የሚሰሩት አዲስ አበባ ላይ ብቻ በመሆኑ የአገሪቱን ባህልና እሴት ማንጸባረቅ አይችሉም'' ብለዋል። በፊልሞች ላይ ኢትዮጵያዊነት ጎልቶ እንዳይወጣም እንደ ችግር የሚገለፀውም በአንድ አካባቢ ብቻ በመታጠሩ መሆኑን አመልክተዋል። ስለሆነም  የፊልም ባለሙያዎች ከአዲስ አበባ ወጥቶ ያልተበረዙ ባህሎች ላይ ትኩረት አድርገው ቢሰሩ ኢትዮጵያውነትን ማንጸባረቅ ይችላሉ ብለዋል አቶ ዳግም። ይህንም ለማድረግ በመንግስት በኩል አስፈላጊውን ድጋፍ መደረግ ይገባዋል ነው ያሉት። የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር አበበ ቀጸላ በበኩላቸው አሁን ያሉት ወጣቶች በዘርፉ በርካታ ስራዎችን ማከናወን ይችላሉ ነገር ግን ባለሙያዎችም  ኢትዮጵያዊነት ባህሪ ያለው ፊልም  ለመስራት ስለ ሀገራቸው በቂ እውቀት መያዝ ይገባቸዋል ብለዋል። እንደ መምህር አበበ ገለጻ ''ኢትዮጵያዊነት በተለያዩ መንግስታት የተለያዩ ስያሜ ሲሰጠው ቆይቷል፤ ይህን አስታርቆ  የሁሉም ዜጋ አሻራ ያላት ሀገርን በፊልሞች ውስጥ  ለማሳየት ድጋፉ አስፈላጊ ነው።'' መንግስት የገንዘብ ፣አቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠትና በሌሎች መስኮችም ድጋፍና እገዛ እንዲያደርግም የውይይቱ ተሳታፊዎች ጠይቀዋል። ከአካል ጉዳተኞች ማህበር የመጡት ወይዘሮ በእምነት አየለ በበኩሏ ፊልሞች ኢትዮጵያዊነትን የሚያንጸባርቁና ሁሉንም የህብረሰተብ ክፍሎች ያማከሉ ሊሆኑ እንደሚገባ ገልጻለች። በአሁኑ ወቅት የሚሰሩት አብዛኞቹ የአማርኛ ፊልሞች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያላደረጉ እንደሆኑ ጠቁመዋል። ኢትዮጵያዊነት ባህሪ ያላቸው ፊልሞች እንዳይሰሩ ካደረጉ ችግሮች መካከል የአሰራር ስርዓት አለመኖሩ፣ የዶክመንት እጥረትና የፖሊሲዎች አተገባበር ችግሮች መሆናቸውን  የገለጸው ደግሞ አርቲስት ደሳለኝ ሀይሉ ነው። ችግሮች ተቀርፈው  ፊልሞቻችን በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን መሰራት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊነት ባህሪ እንዲኖራቸው በቀጣይ ሌሎች ጥናቶችና ውይይቶችን ማካሄድ እንደሚገባ አርቲስቱ ገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም