ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የሀይማት ተቋማት ከጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ግንቦት 7/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት በሰላም፣ በማኅበራዊ ደኅንነት፣ በሥነ ምግባርና በዘላቂ ልማት በጋራ ስለሚሠሩበት ሁኔታ ውይይት ማድረጋቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ገለጹ ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ እንደገለጹት፤ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፣ ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ ከኢትዮጵያ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤትና ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን አባቶች ጋር ተወያይተዋል ።

በውይይቱ ላይ በእምነት ተቋማት መካከል አልፎ አልፎ የሚከሠቱትን ችግሮች በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚያስችል መንገድ ለመዘርጋት፣ የሕዝቡን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች አቅምን አቀናጅቶ ለመፍታት፣ ለአደጋ ጊዜ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ ጠንካራ ተቋም በጋራ ለማቆም፣ ተወያይተዋል።

በተጨማሪም በሕዝቦች መካከል መግባባትና አንድነት ለማምጣት ተቀናጅቶ ለመሥራት፣ ድህነትን ለመቅረፍ የሚያስችሉ የልማት ሥራዎችን በትብብር ለማከናወን፣ እንዲሁም የትውልዱን ሥነ ምግባር በጋራ ለመቅረጽ ሐሳብ መለዋወጣቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተዋል።

የእምነት ተቋማት ያላቸውን መዋቅር ፣ ተሰሚነት፣ የሰው ኃይልና ተጽዕኖ ፈጣሪነት በጋራ ካቀናጁ ብዙ ችግሮች መቅረፍ እንደሚችሉም አስረድተዋል።

ይሄን እውን ለማድረግ ልዩነትን አክብሮ፣ የፖለቲካና የእምነት ድንበሮችን ጠብቆ፣ ነገር ግን ተጋግዞና ተናብቦ መሥራት ይገባል ሲሉ የሃይማኖት አባቶቹ አስተያየት መስጠታቸውንም ዶክተር አብይ ተናግረዋል።

ከትናንት ይልቅ ዛሬና ነገ ላይ ማተኮር፣ ከግጭቶች ይልቅ በጋራ ዕሴቶቻችንና አቅሞቻችን ላይ መተባበር ኢትዮጵያ ዛሬ የምትፈልገው ነው የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ።

የእምነት ተቋማት በተቋም ምሥረታ ያላቸውን ልምድ በመጠቀም፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በአደጋ ሥራ አመራር፣ በድህነት ቅነሳ፣ በርዳታና በሥነ ምግባር ግንባታ ላይ የሚያተኩሩ ጠንካራ ሀገራዊ ተቋማትን በጋራ ቢመሠርቱ፤ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ እንደሚተርፉ እምነቴ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም