በቤንሻንጉል ጉሙዝ አዋጁን የተላለፉ 1 ሺህ 209 ሰዎች ተቀጡ - ኢዜአ አማርኛ
በቤንሻንጉል ጉሙዝ አዋጁን የተላለፉ 1 ሺህ 209 ሰዎች ተቀጡ
አሶሳ፣ ግንቦት 7 /2012 ዓ.ም (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የተላለፉ 1 ሺህ 209 ግለሰቦች መቀጣታቸውን በክልሉ የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ኃይል ገለጸ፡፡
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነርና የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ዓብይ ኮሚቴ አባል መሃመድ ሃመደኒል ለኢዜአ እንደተናገሩት ህብረተሰቡ ራሱን ከኮሮና ቫይረስ እንዲጠብቅ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
ከግንዛቤ ፈጠራው በተጓዳኝ ባለፈው እንድ ሳምንት አዋጁን የተላለፉ 683 የሚኒባስ፣ ባጃጅ እና ሞተር ብስክሌት አሽከርካሪዎች እያንዳንዳቸው ከ600 እስከ 3 ሺህ ብር በሚደርስ ገንዘብ መቀጣታቸውን ተናግረዋል፡፡
አሽከርካሪዎቹ ቅጣቱ የተላለፈባቸው ትርፍ በመጫናቸው ነው ብለዋል፡፡
በጠባብ ቤት ውስጥ ተከማችተው ጫት ሲያስቅሙና ሲቅሙ የተገኙ 135 ሰዎች ደግሞ የገንዘብ ቅጣት እንደተጣለባቸው ኮሚሽነሩ ተናግረዋል ።
በተጨማሪም ምክንያት የሌለው የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ 391 ነጋዴዎች ድርጅታቸውን ከማሸግ ጀምሮ በገንዘብ መቀጣታቸውን አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪም ቤንዚን በጥቁር ገበያ ሲሸጥ የተደረሰበት አንድ የነዳጅ ማደያ ባለቤት ጨምሮ አዋጁን የተላለፉ ሌሎች 180 ሰዎች ደግሞ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
58 መጠጥ ቤቶችና ግሮሰሪዎችም አዋጁን ተላልፈው በመገኘታቸው የታሸጉ ሲሆን ባለቤቶቹ ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑን ገልፀዋል ።