የምርምር ተቋማትና ግለሰቦች ኮቪድ 19 መከላከያ መሳሪያዎችን ለመስራት የሚያደርጉት ጥረት የሚበረታታ ነው

58

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 6/2012 (ኢዜአ) የምርምር ተቋማትና ግለሰቦች ኮቪድ 19 መከላከያ መሳሪያዎችን ለመስራት የሚያደርጉት ጥረት የሚበረታታ መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም ተናገሩ።

የኮቪድ 19 በኢትዮጵያ ከተከሰተ ጀምሮ የአገር ውስጥ የምርምር ተቋማትና ግለሰቦችም ጭምር ቫይረሱን ለመከላከል የሚረዱ መሳሪያዎችን ለመስራትና ለፈጠራ ስራዎች ይበልጥ የተነሳሱበት ሁኔታ መፈጠሩን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

አሁን የገጠመውን ዓለም አቀፋዊ ወረርሽኝ ለማለፍ ሁሉም አካል የበኩሉን መወጣት እንዳለበትም ተናግረዋል።

 መንግስት በዘርፉ የሚደረጉ ምርምርና ጥናቶችን ለመደገፍ የሚያስችል አሰራርና ለጥናትና ምርምር ስራ የሚውል በጀት ማዘጋጀቱንም ተናግረዋል።

በዚህም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ጨምሮ ሌሎች የምርምር ተቋማት የሚያደርጉት ጥናት የሚበረታታ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በዘርፉ የተሰማሩ ማናቸውም ተቋማት ዝርዝር መረጃውን ከቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር ድረ ገፅ ላይ በማዬት መወዳደር እንደሚችሉም ገልጸዋል።

በሚያቀርቡት ፕሮጀክት አሸናፊ ለሚሆኑ ተመራማሪዎች መንግስት ድጋፍ የሚያደርግበት ስርዓት ዘርግቷል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም