ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ዘመናዊ የቆጣሪ ንባብ ሥርዓት ሊተገበር ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዘመናዊ የቆጣሪ ንባብ ሥርዓት ተግባራዊ ሊያደርግ መሆኑን አስታወቀ።

ሥርዓቱ የኃይል በክነትን የሚቀንስ፤ ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን ያስቀራል።

አገልግሎቱ  ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው ሥርዓቱ ከቆጣሪ ንባብ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮችን የሚፈታ አዲስ ቴክኖሎጂ ነው።

ሥርዓቱ ከዚህ ወር አጋማሽ ጀምሮ በመላው አገሪቱ በተመረጡ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት በሙከራ ደረጃ ይተገበራል።

ሥርዓቱ የሚተገበርበት ቴክኖሎጂ 416 ሺህ ዶላር ወጪ የተደረገበት ሲሆን፤ ከ2 ነጥብ 48 ሚሊዮን በላይ የድህረ ክፍያ ተጠቃሚ ደንበኞች ይሆኑበታል።

ዘመናዊና በቆጣሪ ንባብ ላይ የሚነሱ የጥራትና ግምታዊ አሞላል ችግሮችን እንደሚያስቀርም አገልግሎቱ አመልክቷል።

የቆጣሪ አንባቢው በደንበኛው ቤት በአካል ተገኝቶ ትክክለኛ ንባብ መውሰዱ ወይም አለመውሰዱን ሥርዓቱ እንደሚያረጋግጥ ተገልጿል።

በቆጣሪ ንባብ ወቅት የማንበቢያ መሠሪያው የቆጣሪ አንባቢው ደንበኛ ቤት መድረሱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ (ጂፒኤስ) በማረጋገጥ የንባብ መሙያውን ሣጥን አረንጓዴ በማሳየት እንዲሞላ ይፈቅዳል።

አንባቢው በቦታው ካልተገኘ የንባብ መሙያው ሳጥን ቀይ ስለሚያሳይ፤ ግዴታ አንባቢው በደንበኛው ቤት ሄዶ እንዲያነብ ያስገድደዋል ብሏል አገልግሎቱ በመግለጫው።

ቴክኖሎጂው በራሱ የሚያነብ፤ በእጅ ሲነበብ የሚፈጠሩ ስህተቶችን የሚያስቀርና በንባብ ወቅት ምን ያህል ደንበኞች ተደራሽ መደረጋቸውን እንደሚያሳውቅ ተገልጿል።

በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከተጀመረ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ አስቆጥሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም