በዓለም አቀፉ ስመጥር የቡና ቅምሻና ጨረታ ውደድር 40 የኢትዮጵያ የቡና አይነቶች ተመረጡ - ኢዜአ አማርኛ
በዓለም አቀፉ ስመጥር የቡና ቅምሻና ጨረታ ውደድር 40 የኢትዮጵያ የቡና አይነቶች ተመረጡ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 6/2012 (ኢዜአ) በዓለም አቀፍ ደረጃ በተዘጋጀው "በኢትዮጵያ ካፕ ኦፍ ኢክሰለንስ" ውድድር ከተሳተፋ ቡና አምራቾች መካከል 40 የኢትዮጵያ የቡና አይነቶች መመረጣቸውን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ገለጸ። በቀጣይም አምራቹንና አገሪቷን በማስተዋወቅ ከዘርፉ መገኘት ያለበትን ጥቅም ለማግኘት እንደሚረዳ ተገልጿ።
በኢትዮጵያ ካፕ ኦፍ ኢክሰለንስ ውድድር ከተሳተፉት የአገር ውስጥ ቡና አምራቾች መካከል 40 የቡና አይነቶች መመረጣቸውን ባለስልጣኑ ገልጿል።
ከፊድ ዘ ፊውቸር ኢትዮጵያ፣ ቫልዩ ቼይን አክቲቪቲ እና አልያንስ ፎር ኮፊ ኤክሰለንስ ጋር በመተባበር የ2012 ዓ.ም ውድድር መዘጋጀቱን የቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ ገልጸዋል።
ከዚህ በፊት በተካሄዱ መሰል ዓለም አቀፍ ውድድሮች ከ900 በላይ ተወዳዳሪዎች ቀርበው እንደማያውቁና በኢትዮጵያ ግን ከ1 ሺህ 459 በላይ አምራቾች መሳተፋቸው ተገልጿል።
ለውድድር የቀረቡትን የቡና አይነቶች ጣዕም ለመለየት ወደ አሜሪካ ፖርትላንድ መላካቸው ተገልጿል።
ከዚህ በፊት የመጀመሪያው ዙር ምርጫ በአገር ውስጥ ባለሙያዎች የሚከናወን ሲሆን ቀጣዮቹ ምርጫዎች ከ 25 ባላነሱ ዓለም አቀፍ የቡና ቀማሾች እንደሚከናወን ተገልጾ ነበር።
ነገር ግን በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ሁሉም ምርጫ በአሜሪካ ፖርትላንድ ከተማ መደረጉ በመግለጫው ተመላክቷል።
በዚህም በመጀመሪያው ዙር ውድድር 150 የቡና አይነቶች ተለይተው በቀጣይ በተደረጉ ማጣሪያዎች 40 የቡና አይነቶች ከ87 በመቶ በላይ ነጥብ በማስመዝገብ ተመርጠዋል።
ከነዚህም ውስጥ 3ቱ ከ90 በመቶ በላይ ውጤት በማስመዝገብ የኤክሰለንስ አዋርድ አግኝተዋል።
ኢትዮጵያ ካሁን በፊት የቡና ምርት ኤክስፖርት ታደርግባቸው የነበሩ አገራት ውስን በመሆናቸው ውድድሩ ምርቷን በስፋት ለማስተዋወቅ እንደሚረዳት ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
በውድድሩ አሸናፊ የሆኑ ቡና አይነቶች በአለም አቀፍ ደረጃ በኦንላይን ለጨረታ የሚቀርቡ ሲሆን በቡና ገበያ ከፍተኛ የተባለው ዋጋ ይሰጣቸዋል።
በካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ የሚሳተፉ ገዥዎች ቁጥርም ከዚህ በፊት ከተመዘገበው አንፃር በክብረወሰን ደረጃ ከ135 በላይ ገዥዎች በኦንላይን ተመዝግበው ሰኔ 18 ቀን 2012 ዓ.ም የሚካሄደውን ጨረታ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ተመላክቷል።
የቡና ዘርፍ ከካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ውድድር ብዙ ጥቅሞችን እንደሚያገኝና አሸናፊ የሆኑ የቡና አይነቶች በጥራታቸው በመታገዝ ከፍተኛ ክፍያ ያገኛሉ ተብሏል።
በተጨማሪም ተቋሙ በሚያዘጋጃቸው ስመጥር የውድድር መድረኮች ላይ በስፋት የመተዋወቅ ዕድል ያገኛሉ ብለዋል።
የግብይት ሂደቱ ቀጥተኛ በመሆኑ የቡና አምራቹን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የቱሪስት ፍሰቱን እንደሚጨምርና የአገር ገጽታን በመገንባት በኩል የላቀ ሚና አለው ተብሏል።
የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ፕሮግራም ከ1991 ዓ.ም አንስቶ ገበሬዎች ከሚያመርቱት ቡና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የራሱን መስፈርት በማውጣት እየሰራ የሚገኝ ዓለም አቀፍ ተቋም ነው።
ውድድሩ መካሄድ ከጀመረ 20 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን ኢትዮጵያ የቡና አምራች አገር ብትሆንም በውድድሩ ስትሳተፍ የመጀመሪያ ጊዜዋ መሆኑ ተጠቅሷል።