ቀጥታ፡

''የፖሊስ የዘፈቀደ እስር በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል'' - ኮሚሽኑ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6/2012 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ የተገኙ ሰዎች እስር በአስቸኳይ እንዲቆም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ ጠየቁ። ኮሚሽኑ ''የዘፈቀደ እስር'' ባለው እርምጃ የታሰሩትም ይለቀቁ ብሏል።

ዋና ኮሚሽነሩ እንደገለጹት ፖሊስ በከተማው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ያላደረጉ ባላቸው ነዋሪዎች ላይ የወሰደው እርምጃ ተገቢነት የለውም።

“የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ የኮቪድ 19 ስርጭትን ለመከላከል አስፈላጊ የጤና መመሪያና ኅብረተሰቡ ሊከተለው የሚገባ ነው'' ብለዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ ደንቡ ማንኛውም ሰው በገበያ፣ በሱቆች፣ በትራንስፖርት አገልግሎት ባሉ የሕዝብ አገልግሎት መስጫ ቦታዎችና በሌሎች ሕዝብ በሚበዛባቸውና የአካል መራራቅን መጠበቅ በማይቻልባቸው አካባቢዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ እንዳለበት እንደሚደነግግ ተናግረዋል።

ከዚህ ውጭ ግን በየትኛውም ቦታ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ የተገኙ ሰዎች ሁሉ ላይ የሚደረግ የዘፈቀደ እስር ከሕግ ውጭ ከመሆኑም በላይ፤ ለነገሩ ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃና የታለመለትን ዓላማ ይቃረናል በማለትም ዋና ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።

በመሆኑም ድርጊቱ  በአስቸኳይ ሊቆምና በዚህ ሁኔታ የታሰሩ ሰዎችም በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቀዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ትናንት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛውን ያላደረጉ ከ1ሺህ 300 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ሥር አውሎ በምክር ለቋቸዋል።

ሰዎቹ የተያዙት ሕዝብ በተሰበሰበባቸው ቦታዎች መሸፈኛውን ሳያደርጉ በመንቀሳቀሳቸውና ርቀታቸውን ባለመጠበቃቸው እንደነበር ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም