ቀጥታ፡

በወልድያ ከተማና ምስራቅ ሐረርጌ ዞን ለተቸገሩ 5ሺህ 400 ወገኖች የምግብ እህል ድጋፍ ተደረገ

ወልድያ/ ሐረር /ደሴ/ ጎንደር/ ግንቦት 6 /2012 (ኢዜአ ) በወልድያ ከተማና ምስራቅ ሐረርጌ ዞን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙና አቅመ ደካማ ለሆኑ 5ሺህ 400 ወገኖች የምግብ እህል ድጋፍ ተደረገ።

በወልድያ ከተማ ድጋፉን ያደረጉት  አንድ ባለሀብት አንድ ሚሊዮን 400ሺህ ብር በሆነ ወጪ የምግብ ዱቄት ነው። 

ባለሃብቱ  አቶ ሃጂ ሲራጅ አደም በተወካያቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት የምግብ ዱቄት ድጋፍ የያደረጉት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለተቸገሩ ወገኖች መሆኑን ገልጸዋል።

በወልድያ ከተማና አካባቢው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ  4ሺህ 900  የህብረተሰብ ክፍሎች 500 ኩንታል ዱቄት ገዝተው ማከፋፈላቸውንም አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል በውጭ የሚኖሩ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የወተር ከተማ ተወላጆች ለ500 አቅመ ደካሞች የምግብ እህል ድገፍ አድርገዋል።


የድጋፉ አስተባባሪ  ወጣት ያደታ ጁንዲ እንደገለጸው ቫይረሱ ባስከተለው ተጽዕኖ በከተማው ለችግር የተጋለጡ ወገኖች ያደረጉት ድጋፍ ከ700 ሺህ  ብር በላይ የሚያወጣ ሩዝ፣  የዱቄት እህል እና የምግብ ዘይት ነው።


የወተር ከተማ አስተዳዳሪና የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አስተባበሪ  አቶ አህመዲን መሀመድ በውጭ የሚኖሩ 200 የሚሆኑ የአካባቢው ተወላጆች ላደረጉት የበጎ አድራጎት ስራ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል የከተማው ቀበሌ  አንድ  ነዋሪ ወይዘሮ አዜብ ታፈሰ  ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።

በተያያዘ ዜና በደሴ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የሁለት ክፍለ ከተሞች በጎ ፋቃደኛ ወጣቶች ከ260 ሺህ ብር በላይ በማሰባሰብ ለአቅመ ደካሞች የምግብ እህል በመግዛት  ድጋፍ  አድርገዋል።

የአራዳ ክፍለ ከተማ ዋና ስራአስኪያጅና የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባል አቶ ሽመልስ ሰይፉ በበኩላቸው  "የተደረገው ድጋፍ የምግብ እህል፣ ዱቄት፣ ሩዝ፣ መኮረኒ፣ ፓስታ፣ ሽሮና በርበሬ ይገኝበታል" ብለዋል።

በቀጣይም ችግረኞችን ለመርዳት ግማሽ ሚሊዮን ብር የሚገመት ቁሳቁስ መሰብሰቡን አውስተው በቅርቡ ለማሰራጨት በየቀበሌው የተቸገሩ ወገኖች የመለየት ስራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

በመናፈሻ ክፍለ ከተማ የቀለም ሜዳ ቀበሌ አስተዳደሪና የግብረ ኃይሉ አባል  አቶ ቢያድግልኝ ዮሐንስ በበኩላቸው ከበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የተገኘው ድጋፍ  ለአካል ጉዳተኞችና አረጋዊያን መሰጠቱን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የደባርቅ ዩንቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ከአራት ሚሊየን ብር በላይ መድቦ እየሰራ መሆኑን የዩንቨርሲቲው የአስተዳደርና የተማሪዎች ጉዳይ ምክትል ፕሬዘዳንት ዶክተር አስማረ መለሰ ገልጸዋል።

ዩንቨርሲቲው በደባርቅና አካባቢው ለሚገኙ አምስት የጤና ተቋማት የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች፣ የእጅ ማስታጠቢያዎችና የሰውነት ሙቀት መለኪያ መሳሪያዎች ድጋፍ ማድረጉን አውስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም