ቀጥታ፡

ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ የስራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን የጃፓን አምባሳደር አሰናበቱ

አዲስ አበባ ሰኔ 28/2010 የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የስራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን የጃፓን አምባሳደር ሺንቺ ሳይዳን አሰናብተዋል። በኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት የቆዩት አምባሳደር ሺንቺ ሳይዳ በኢትዮጵያ ቆይታቸው የሁለቱ አገራትን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ሲሰሩ መቆየታቸው ተገልጿል። ጃፓን በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የተለያየ አስተዋፆ ከሚያበረክቱ አገራት መካከል የምትጠቀስ ሲሆን፤ የአገሪቷ አስተዋጽፆ በኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ልማት፣ በግብርና እና ገጠር ልማት እንዲሁም በሰው ኃይል ልማት ላይ በሚደረጉ ድጋፎች ጋር የተያያዘ ነው። ፕሬዚዳንቱ በጽህፈት ቤታቸው ከአምባሳደሩ ጋር በነበራቸው ቆይታ ጃፓን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል። ውይይቱን የተከታተሉት የፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት የፕሮቶኮልና የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሸበር ጌትነት ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ 'የሁለቱ አገራት ጠንካራ ግንኙነት በተተኪው አምባሳደር እንዴት ማስቀጠል ይቻላል?' በሚለው ጉዳይ ላይ ውይይት ማድረጋቸውን ገልፀዋል። በጃፓን ድጋፍ ሲሰሩ ከቆዩ ተግባራት መካከል በከፍተኛ ቦታዎች የሚገኙ የበግ ቆዳዎችን ጥራት በማሳደግ የሚመረቱ ጫማዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ማስቻልና የኢትዮጵያን ስም ማሳደግ የሚሉና ሌሎች ድጋፎች በቀጣይ እንደሚሰሩ ነው አቶ አሸብር የሚገልፁት። አምባሳደር ሺንቺ ሳይዳ በበኩላቸው በነበራቸው ቆይታ የኢትዮጵያና ጃፓን ግንኙነት የበለጠ እንዲጠናከር ሲሰሩ መቆየታቸውን በመግለጽ የጃፓን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ለማድረግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል። ተሰናባቹ አምባሳደር በኢትዮጵያ ለነበራቸው መልካም ቆይታ ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን የሁለቱ አገራት ግንኙነትን ለማሳደግ እንደሚሰሩና ለአገሪቱም ሰላምና ብልጽግናን ተመኝተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም