በትግራይ የማኅበረሰብ እንክብካቤ ጥምረቶች አቅመ ደካሞችን እያገዙ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ የማኅበረሰብ እንክብካቤ ጥምረቶች አቅመ ደካሞችን እያገዙ ነው
መቀሌ፣ ግንቦት 06/12 (ኢዜአ) በትግራይ የሚገኙ የማኅበረሰብ እንክብካቤ ጥምረቶች የኮሮና ስርጭትን ለመግታት በሚደረገው ጥረት አቅመ ደካሞችን በማገዝ ጉልህ ሚና በመጫወት ላይ መሆናቸውን ገለጹ።
በትግራይ ክልል በሁሉም ወረዳዎች በኅብረተሰቡ ፍላጎት የተቋቋሙ የማኅበረሰብ እንክብካቤ ጥምረቶች የአቅመ ደካሞችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ለመቅረፍ ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
በክልሉ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የማኅበረሰብ ደህንነት ጥበቃና ልማት ማስፋፊያ ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ተክለሃይማኖት ገብረመስቀል እንዳሉት በክልሉ በሚገኙ ከ800 በላይ የገጠር ቀበሌዎች የተቋቋሙ ጥምረቶች ችግረኞችን በመርዳት ላይ ናቸው።
ከግማሽ ሚሊዮን በላይ አባላት ያሏቸው እነዚሁ ጥምረቶች ሰብዓዊ ድጋፋቸውን በማጠናከር የኮሮና ቫይረስ በመከላከሉ ሂደት ጉልህ ሚና በመጫወት ላይ እንደሚገኙ አቶ ተክለሃይማኖት ገልጸዋል።
ቢሮው በክልሉ በተቋቋመው ግብረ ኃይል የማኅበራዊ ልማት ዘርፍ ንዑስ ኮሚቴ አባል በመሆኑ ጥምረቶቹ የሚያደርጉትን ድጋፍ በማስተባበር ላይ እንደሚገኝ ገልጸው በአላማጣ ከተማ፣ በሕንጣሎ ዋጅራትና በክልተ አውላዕሎ የሚገኙ ጥምረቶች ያደረጉትን ድጋፍ በማሳያነት ጠቅሰዋል።
በአላማጣ ከተማና በሕንጣሎ ዋጀራት የሚገኙ የማኅበረሰብ እንክብካቤ ጥምረት አባላት ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ቁሳቁሶችን በማሰባሰብ ለአቅመ ደካሞች ማከፋፈላቸውን ተናግረዋል።
የአላማጣ ከተማ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ፀጋ ገብረማሪያም እንደገለጹት በከተማው የሚገኙ አራት የማኅበረሰብ እንክብካቤ ጥምረቶች የኮሮና ቫይረስ ተፅዕኖ ላሳደረባቸው አንድ ሺህ ችግረኞች 89 ኩንታል እህልና 90 ሺህ ብር ጥሬ ገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል።
በትግራይ ምሥራቃዊ ዞን በክልተ አውላዕሎ ወረዳ በ19 የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ የሚገኙ የማኅበረሰብ እንክብካቤ ጥምረት አባላት ደግሞ ከ87 ሺህ ብር በላይ በማሰባሰብ ሦስት ሺህ ለሚጠጉ አቅመ ደካሞች ድጋፍ ማድረጋቸውን የወረዳው የቅድመ ማስጠንቀቂያና ዝግጁነት ንዑስ ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ አሸናፊ ገብረሚካኤል ተናግረዋል።