ቀጥታ፡

ሲኖዶሱ መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲቀጥል ወሰነ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከዛሬ ጀምሮ መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲቀጥል ውሳኔ አሳለፈች። የፖለቲካ ኃይሎች ለአገራዊ ሰላምና ለአንድነት እንዲቆሙም ጠይቃለች።

የቤተ ክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ የሶስት ቀናት ጉባዔው ሲያጠናቀቅ መግለጫ ሰጥቷል።

የቤተ ክርስቲያኗ ፓትርያርክ ብጹዕ አቡነ ማቲያስ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተቋረጠው መንፈሳዊ አገልግሎት ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እንዲጀመር ሲኖዶሱ ወስኗል።

በወረርሽኙ ሳቢያ በየአጥቢያ ዐብያተ ክርስቲያናት የሚሰጠው አገልግሎት መቋረጡ በምዕመናን መንፈሳዊ ሕይወት ላይ ችግር መፍጠሩና ምዕመናን ከቤተክርስቲያን መለየት አገልግሎቱ እንዲቀጥል መወሰኑንም ገልጸዋል።

አገልግሎቱ በቀጣይ የምዕመናን ጤና በጠበቀ መልኩ ከሃይማኖት አባቶችና ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጠውን ሙያዊ ምክር በመከተል እንደሚካሄድም ተመልክቷል።

በተለይ መንግሥት የኮቪድ 19 ወረርሸኝን ለመከላከል የሚሰጠውን መመሪያ መሠረት በማድረግ፣ ርቀትንና ንፅህናን መጠበቅ እንደሚያስፈልግም ተገልጿል።

ቤተ ክርስቲያኗ በሽታው በፈጣሪ በምሕረት እንዲያጠፋ ስትፀልይ የቆየች ሲሆን፣ በቀጣይም ካህናትም ሆኑ ምዕመናን ይህንኑ እንዲያጠናከሩ ሲኖዶሱ አሳስቧል።

 ምዕመናን ''አስከፊና ፈታኝ'' የሆነውን ወቅት በመረዳዳትና በመተሳሰብ እንዲያሳልፉትም ጠይቋል።

በሌላው በኩል ደግሞ ሲኖዶሱ በመላው አገሪቱ የሚገኙ የፖለቲካ ኃይሎች ለአገራዊ ሰላምና ለሕዝባዊ አንድነት እንዲቆሙም ጥሪ አስተላልፋለች።

ሲኖዶሱ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን የደረሰበትን ደረጃ በአድናቆት እንደሚመለከተው አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም