በደብረ ብርሀን ከተማ የአዋጁን ድንጋጌ ተላለፈው የተገኙ ግለሰቦች በእስራት ተቀጡ - ኢዜአ አማርኛ
በደብረ ብርሀን ከተማ የአዋጁን ድንጋጌ ተላለፈው የተገኙ ግለሰቦች በእስራት ተቀጡ
ደብረ ብርሀን፣ ግንቦት 6/ 2012 (ኢዜአ)የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል መንግስት የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌ ተላልፈው ተገኝተዋል የተባሉ ግለሰቦች በእስራት እንዲቀጡ መወሰኑን የከተማው አስተዳደር ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አስታወቀ።
የግብረ ኃይሉ አባልና የአስተዳደሩ ፍርድ ቤት ዳኛ ወይዘሮ ሰርካለም ደባይ ለኢዜአ እንገደለጹት በእሰራት እንዲቀጡ ከተወሰነባቸው መካከል ልጁን ለመዳር ሰርግ ደግሶ የተገኘ ግለሰብ ይገኝበታል።
ግለሰቡ ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ሰርግና መሰል ማህበራዊ ክልከላዎች የተደነገጉ ቢሆንም ይህንን ቸላ በማለት ሚያዚያ 29/2012ዓ.ም ድግስ አዘጋጅቶ ከ50 በላይ ሰዎችን ሰብስቦ ሴት ልጁን መዳሩን አስረድተዋል።
ጉዳዩን የተመለከተው የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤት ግንቦት 4/2012ዓ.ም በዋለው ችሎት ግለሰቡ በቀረበበት ማስረጃ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ በሁለት ወር እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን አስታውቀዋል።
እንዲሁም አንድ ሌላ ግለሰብ የአዋጁን የክልከላ ድንጋጌ በመለተላለፍ በጭነት ተሽከርካሪ ላይ 11 ሰዎችን አሳፍሮ ሲያጓጉዝ በመገኘቱ በአንድ ወር ከ15 ቀናት እንዲቀጣ መወሰኑን ዳኛዋ ገልጸዋል።
ፍርድ ቤቱ ካለፈው ወር መጨረሻ ጀምሮ ርቀታቸውን ሳይጠብቁ ሲንቀሳቀሱ ፣ ከተፈቀደላቸው በላይ ሰው አሳፍረው የተገኙ አሽከርካሪዎችና መሰል የህግ መጣስ ተግባር የፈጸሙ 30 ሰዎች ክስ ተመስርቶባቸው በእስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ መወሰኑን ከፍርድ ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።