ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር 8 ሚሊዮን 700ሺህ ብር ግምት ያለው ቁሳቁስ አከፋፈለ

ሀዋሳ / ሽሬ/ መተማ / ግንቦት 5/2012(ኢዜአ) .የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ኮሮናን ለመከላከል የሚረዳ ስምንት ሚሊዮን 700ሺህ ብር ግምት ያለው ቁሳቁስ በደቡብ ክልል ለሚገኙ ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች አከፋፈለ። 

በተመሳሳይ በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን  ግለሰቦችና ድርጅቶች እንዲሁም የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ  ከ460ሺህ  ብር በላይ የሚገመት ምግብና ቁሳቁስ አበረከቱ።

በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር  የደቡብ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተሾመ ታከለ እንደገለጹት ማህበሩ  ስምንት ሚሊዮን 700ሺህ ብር ግምት ያለው የንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘርና የእጅ ሳሙና በክልሉ ዞኖችና  ከተማ አስተዳደሮች በሚገኙ የማህበሩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች አማካኝነት አከፋፍሏል።

የተከፋፈለውም ኮሮናን ለመከላከልና  ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ለሚያስጨብጡ ለተሰማሩ  ከ361 ሺህ በላይ በጎ ፍቃደኞች እና  ለህክምና ተቋማት አገልግሎት እንዲውል መሆኑን አቶ ተሾመ አብራርተዋል።

የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባልና የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ አባተ በበኩላቸው ግብረ ኃይሉ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ባለው የሀብት ማሰባሰብ ሥራም 285 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ በጥሬ ገንዘብና በዓይነት  ድጋፍ መገኘቱን ገልጸዋል።

የተገኘው ድጋፍም ቀይ መስቀልን ጨምሮ  ከተለያዩ ለጋሽ አካላትና ግለሰቦች መሆኑን አመልክተዋል።

በተመሳሳይ በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ከ318 ሺህ ብር በላይ የሚገመቱ የምግብና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ድጋፍ  መደረጉን የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የቫይረሱ መከላከልግብረ ኃይል አስተባባሪ አቶ ሃፍቶም ፋንታሁን  አስታውቁ።

በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ካሉ በጎአድራጊ ግለሰቦችና ድርጅቶች የተበረከተው ይሄው ድጋፍ በአካባቢው  በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ወገኖች መከፋፈሉንም ተናግረዋል።

በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ድጋፉን ካገኙት መካከል ወይዘሮ ሙሉ ተስፋዬ በሰጡት አስተያየት  የተሰጣቸው 25 ኪሊግራም የዳቦ ዱቄት እና የንጽህና መጠበቂያ  ከሁለት ልጆቻቸውን ጋር እንደሚጠቀሙበት ተናግረዋል።

የሰው ልብስ አጥበው የሚያገኙት የእለት ገቢያቸው በቫይረሱ ምክንያት በመቆሙ ያጋጣማቸውን ችግር ለማቃለል የተሰጣቸው 25 ኪሎ ግራም የዳቦ ዱቄት እንደሚረዳቸው ገልጸዋል።

በዞኑ ቀደም ሲልም ከተለያዩ በጎ አድራጊዎች በተገኘ  ከአንድ ሚሊዮን 400ሺህ ብር የተገዛ 480 ኩንታል የዳቦ ዱቄት ለአንድ ሺህ 920 ችግረኛ ወገኖች መከፋፈሉም ተመልክቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ  ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ከ150ሹህ ብር በላይ ግምት ያለው የቁሳቁስ ድጋፍ  አድርጓል።

በዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ ድጋፍና የኢንዱስትሪ ትስስር ዳይሬክተር አቶ አምባቸው ወረታ እንደተናገሩት

በተቋሙ ከተደረገው ድጋፍ መካከልም ፣ 20 ኩንታል ሩዝ፣ ሶስት ኩንታል በርበሬና  ሁለት ሺህ ሳሙና   ይገኙበታል።

ድጋፉ ከሱዳን  ተመልሰው በማቆያ ቦታዎች ለሚገኙ ዜጎች የሚውል መሆኑን ገልጸዋል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ማህበራዊ ልማት መምሪያ ኃላፊና የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ፀሐፊ ሲስተር ክሽን ወልዴ  ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ  ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም በለይቶ ማቆያ ላሉ 330 ዜጎች  የምግብ፣ መጠጥ፣ ንጽህናና ሌሎች አገልግሎቶች እያቀረበላቸው መሆኑን ጠቁመው  እስካሁን ከተለያዩ ተቋማት አንድ ሚሊየን ብር የሚጠጋ ግምት ያለው የቁሳቁስ ድጋፍ ለለይቶ ማቆያ ቦታዎች መደረጉንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም