ኢትዮ ሊዝ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ 1 ነጥብ 68 ሚሊዮን ብር አበረከተ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮ ሊዝ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ 1 ነጥብ 68 ሚሊዮን ብር አበረከተ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 5/2012(ኢዜአ) ኢትዮ ሊዝ የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ 1 ነጥብ 68 ሚሊዮን ብር አበረከተ።
የውጭ አገር የካፒታል እቃዎች አቅራቢ ድርጅት የሆነው ኢትዮ ሊዝ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ድጋፉን ትናንት የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ለተቋቋመው ብሔራዊ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አበርክቷል።
መንግስት ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያከናውናቸውን እንቅስቃሴዎች የተለያዩ አካላት እንዲደግፉ ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ ኢትዮ ሊዝ የገንዘብ ድጋፉን ማድረጉን ገልጿል።
የኢትዮ ሊዝ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ግርማ ዋኬ እና የኢትዮ ሊዝ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ግሩም ፀጋዬ በጋራ በመሆን በሰላም ሚኒስቴር ተገኝተው ድጋፉን አበርክተዋል።
የኢትዮሊዝ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ግርማ ዋኬ በሥነ-ስርዓቱ ወቅት “ኢትዮ ሊዝ የኮርፖሬት ግዴታውን የሚወጣ ተቋም ነው" ብለዋል።
"የኢትዮጵያ ጉዳይ የእኛ ጉዳይ ነው። ይህ የዛሬው መዋጮ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመዋጋት መንግስት የሚያደርገውን ጥረት ለመደገፍ ያለንን ቁርጠኝነት ያሳያል” ብለዋ።
የኢትዮ ሊዝ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ግሩም ፀጋዬ በበኩላቸው በእንደዚህ ዓይነት የቀውስ ወቅት የግሉ ሴክተር ሚና ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
''አገሪቱ የተጋረጠባትን አደጋ ለማለፍ እየተደረጉ ላሉ እንቅስቃሴዎች የድርጅታችን ድጋፍ እንደማይለይ በዚህ የገንዘብ ድጋፍ ቁርጠኝነታችንን የበለጠ ለመግለጽ እንወዳለን" ብለዋል።
ኢትዮ ሊዝ አፍሪካ አሴት ፋይናንስ ካምፓኒ የተሰኘ ድርጅት ቅርንጫፍ ሲሆን ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ፈቃድ አግኝቶ ባለፈው ሀምሌ በይፋ ስራዉን የጀመረ ተቋም ነው።
በዋነኛነት የተቋቋመውም ከፍተኛ የገንዘብ አቅምን የሚጠይቁ መሳሪያዎችን በማቅረብ ለተለያዩ መስኮች ማለትም ለግብርና፣ ለጤና፣ ኢነርጂ፣ የምግብ ማቀነባበር እንዲሁም ሌሎች የማምረት ተግባራት ላይ እገዛ ለማድረግ እንደሆነ በመግለጫው አመልክቷል።