ድግስ ያዘጋጁና የተሳተፉ አስራ ስምንት ግለሰቦች በገንዘብ ተቀጡ - ኢዜአ አማርኛ
ድግስ ያዘጋጁና የተሳተፉ አስራ ስምንት ግለሰቦች በገንዘብ ተቀጡ
ጅማ ግንቦት 5/2012 (ኢዜአ) በጅማ ከተማ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በመተላለፍ ድግስ ያዘጋጁና ሲሳተፉ የተገኙ አስራ ስምንት ግለሰቦች በገንዘብ ተቀጡ፡፡
በገንዘብ የተቀጡት ግለሰቦቹ መንግስት ኮሮናን ለመከላከል ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አወጅ በመተላለፋቸው መሆኑን የጅማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ገልጿል፡፡
የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባል የሆነው የመምሪያው የኮሙዩኒኬሽን ዲቪዥን ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ገዛሃኝ አውግቸው እንደገለጹት በጅማ ከተማ ቆፊ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ ግለሰብ ግንቦት 02/2012ዓ.ም ድግስ አዘጋጅተው አብረዋቸው የተሳተፉ ጭምር ፖሊስ በደረሰው ጥቆማ መሰረት ተደርሶባቸዋል።
ጉዳያቸውም ተጣርቶ አቃቤ ህግ የመሰረተባቸውን ክስ የተመለከተው የጅማ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ግንቦት 5/ 2012ዓ.ም. በዋለው ችሎት ጥፋተኛ እንደሆኑ መረጋገጡን ዋና ኢንስፔክተር ገዛሃኝ አስረድተዋል።
በጥፋታቸውም ሰባት ሰዎች በ1ሺህ 100 ብር፣ ስድስት ሰዎች በ900 ብር እንዲሁም አምስት ሰዎች ደግሞ በ800 ብር እንዲቀጡ የተወሰነባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
መንግስት አዋጁን ያወጣበት ዋና ዓላማ ለህብተሰቡ ጤንነት መሆኑን ሁሉም ተገንዝቦ ህጉን እንዲያከብርም አሳስበዋል።
እንደ ድገስ ያሉ ማህበራዊ ግንኝነቶች ደግሞ የኮሮና ቫይረስን ስርጭት በማፋጠን በህዝብና ሀገር ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ህብረተሰቡ ሳይዘናጋ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።