በማዕከላዊ ጎንደር በሀሰተኛ የብር ኖት ግብይት ለመፈጸም የነበረ ግለሰብ ተያዘ - ኢዜአ አማርኛ
በማዕከላዊ ጎንደር በሀሰተኛ የብር ኖት ግብይት ለመፈጸም የነበረ ግለሰብ ተያዘ
ጎነደር /ኢዜአ/ ግንቦት 5/2012 በማእከላዊ ጎንደር ዞን ጠገዴ ወረዳ 74 ሀሰተኛ ባለ መቶ የብር ኖቶች በመያዝ ግብይት ለመፈጸም ሙከራ ያደረገው ግለሰብ መያዙን ፖሊስ አስታወቀ፡፡
የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ጀንበር ሙሉ ለኢዜአ እንደተናገሩት ግለሰቡ የተያዘው ትናንት እኩለ ቀን አካባቢ በወረዳው እርጎዬ በተባለው ቀበሌ በሚገኝ የገበያ ስፍራ በሃሰተኛ ብር ፍየል ለመግዛት ሲሞክር ነው፡፡
ህብረሰቡ ለፀጥታ አካላት በሰጠው ጥቆማ ግለሰቡ ከሃሰተኛ የብር ኖቶቹ ጋር እጅ ከፍንጅ ሊያዝ መቻሉን ዋና ኢንስፔክተሩ ተናግረዋል፡፡
በግለሰቡ እጅ የተገኘው የብር ኖት በሰሮቃ ከተማ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባደረገው ፍተሻ ሃሰተኛ መሆኑን መረጋገጡንም አስታውቀዋል፡፡
ግለሰቡ በህግ ቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተካሄደበት መሆኑን ዋና ኢንስፔክተሩ ጠቁመው፤ ህብረሰቡ በግብይት ወቅት መሰል ችግር እንዳይከሰት ጥንቃቄ እንዲያደርግም አሳስበዋል፡፡