የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ተገበያዮች አካላዊ ርቀታቸውን ጠብቀው የሚገበያዩበት የኤሌክትሮኒክስ ግብይት መድረክ አዘጋጀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ተገበያዮች አካላዊ ርቀታቸውን ጠብቀው የሚገበያዩበት የኤሌክትሮኒክስ ግብይት መድረክ አዘጋጀ
አዲስ አበባ ግንቦት 5/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታታት እንዲቻል ተገበያዮች አካላዊ ርቀታቸውን ጠብቀው የሚገበያዩበት የኤሌክትሮኒክስ የግብይት መድረክ ማዘጋጀቱን አስታወቀ።
የኤሌክትሮኒክስ የግብይት መድረኩ ከግንቦት 3 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በስራ ላይ ውሏል።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋናው አርጋ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ስራ ሃላፊዎች በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና መስሪያ ቤት በመገኘት ጉብኝት አድርገዋል።
የሠራተኞችንና የተገበያዮችን ደህንነት በመጠበቅ፣ የኮሮናቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከል እየተሰራ እንደሆነ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኝ ነገራ በጉብኝቱ ወቅት ተናግረዋል።
''ወረርሽኙ እንዳይስፋፋ ጠንካራ የመከላከል እርምጃዎችን እየወሰድን ነው'' ሲሉ ገልጸዋል።
ግብይቱን በኤሌክትሮኒክስ መንገድ ለማካሄድ የሚያስችል የኔትወርክ ዝርጋታ ተካሂዶ በአንድ ጊዜ ከ50 በላይ ተገበያዮችን ማስተናገድ እንዲቻል መደረጉን አስረድተዋል።
እስካሁን ድረስ ምርት ገበያው 40 ተገልጋዮችን በማስተናገድ ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ምርት ገበያው ኮቪድ-19ን ለመከላከል በግብይት ቦታዎችና አካባቢዎች፣ የተገበያዮችን ደህንነት ለመጠበቅ፣ ርቀታቸውን በመጠበቅ እንዲገበያዩ ለማስቻል ቀደም ሲል በፈረቃ ሲሰራ እንደነበርም አስታውሰዋል።
ይሁንና ይህ ተጨማሪ መድረክ መዘጋጀቱ ቀድሞ የነበረውን የፈረቃ አሠራር በማስቀረት ሁሉንም በየዕለቱ ማገበያየት እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ይህ መሆኑ በየቀኑ የሚገበያየውን ምርት መጠን የሚያሳድገው መሆኑን ገልጸው፤ ''የኤሌክትሮኒክስ ግብይት መድረኩ ወደስራ በገባበት የመጀመሪያ ቀን ብቻ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ማገበያየት ተችሏል'' ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የተገበያዮችን አካላዊ ርቅት ለመጠበቅ አዲስ የማቆያ አዳራሽ መዘጋጀቱን ገልጸው፤ ሁሉም ለግብይት የሚመጡ ተገልጋዮች በባለሙያዎች ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋናው አርጋ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ ምርት ገበያው የምርቶች ግብይት ሳይስተጓጎልና የወጪ ንግድ ሥርዓቱ ወደ ኋላ እንዳይመለስ በማድረግ በኩል ትልቅ ሥራ ሰርቷል።
ምርት ገበያው ለዜጎችና ለተገበያዮች ደህንነት ትኩረት በመስጠት የተለያዩ የጥንቃቄና የመከላከል ስራዎችን በማድነቅ፤ ''የግብይት ሥርዓቱ ሙሉ ለሙሉ እንዳይቋረጥና እዳይስተጓጎል መደረጉ ለአገር ኢኮኖሚ ትልቅ አስተዋጾ ያደረገ ነው'' ብለዋል።
ባለፈው መጋቢትና ሚያዚያ ወር የወጪ ንግድ አፈጻጸሙ ያልተቋረጠና ምንም አይነት ጉዳት ሳይደርስበት ማለፍ መቻሉን ጠቅሰው፤ ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።