በጎ አድራጊዎች 230 ለሚሆኑ አቅመ ደካሞች የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
በጎ አድራጊዎች 230 ለሚሆኑ አቅመ ደካሞች የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ
አዳማ፤ ግንቦት 05/2012 (ኢዜአ)በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳማ ወረዳ 230 ለሚሆኑ አቅመ ደካሞች በጎ አድራጊዎች የምግብ እህል፣ ዘይት እና የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረጉ።
የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የዜጎች እንቅስቃሴ መገደቡን ተከትሎ ችግር ላጋጠማቸው ወገኖች ለማገዝ ድጋፉ የተደረገው በወረዳው ወንጂ ሸዋና ወንጂ ዓለም ጤና አካባቢ ለሚገኙ አቅመ ደካማ ነዋሪዎች ነው።
በሀገር ውስጥና ውጭ የሚኖሩ የወንጂ አካባቢ ተወላጆች፣ ባለሃብቶችና የአመራር አካላት ህብረሰተቡን በማስተባበር ድጋፉን አሰባስበው መስጠታቸውን የአዳማ ወረዳ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባል አቶ ከድር ገና ገልጸዋል።
ድጋፉ የተደረገውም አጋዥ የሌላቸው አረጋዊያንና መንቀሳቀስ ተስኗቸው በቤት ውስጥ ለሚገኙ አቅመ ደካሞች መሆኑንም አመልክተዋል።
አቶ ከድር እንዳሉት ከበጎ አድራጊዎቹ የተሰበሰበው የስንዴና በቆሎ ዱቄት፣ ፓስታ፣ የምግብ ዘይትና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ ለእነዚህ ወገኖች እንዲደርሳቸው ተደርጓል።
የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴው አስተባባሪ ወጣት ናትናኤል ሰለሞን በበኩሉ ድጋፉ ከ300 ሺህ ብር በላይ የሚገመት መሆኑን ተናግሯል።
በወንጂ ሸዋና ወንጂ ዓለም ጤና ያሉ አረጋዊያንና አቅመ ደካሞች በ"ፊሎራይድ" ምክንያት የጤና ችግር ያለባቸው ከመሆኑም ባለፈ የገቢ አማራጭ የሌላቸው በመሆኑ ጭምር ድጋፍ እንደተደረገላቸው ገልጿል።
በዘላቂነትም የህክምና ፣የምግብና የአልባሳት ድጋፍ እንዲያገኙ ለማስቻል በስማቸው ማህበር ለማቋቋም ከወረዳው አመራር አካላት ጋር በትብብር እየሰሩ መሆኑንም ወጣት ናትናኤል ተናግሯል።
ድጋፉን ካገኙት መካከል ወይዘሮ የኔነሽ ገብረመድህን በሰጡት አስተያየት በጤና ችግር ምክንያት ተንቀሳቅሰው ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን መርዳት እንደተቸገሩ ገልጸዋል።
"የአካባቢው ተወላጆችና ባለሃብቶች አቅም አጥተን በቤት ውስጥ ለቀረን አቅመ ደካሞች ጉልበት ሆነውናል" በማለት፤ ለተደረገላቸው ድጋፍም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።