ቀጥታ፡

ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የግንባታ መረጃ ሞዴል ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ሊደረግ ነው

አዲስ አበባ ሰኔ 28/2010 በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የግንባታ መረጃ  ቴክኖሎጂ ለመተግበር ዝግጅት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት አስታወቀ። የግንባታ መረጃ ሞዴል በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ተገልጿል። ኢንስቲትዩቱ የግንባታ መረጃ ሞዴል በተመለከተ ዛሬ መግለጫ የሰጠ ሲሆን የአሰልጣኞች ስልጠና የወሰዱ ባለሙያዎችንም አስመርቋል። በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ እንደተናገሩት፤ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ከግብርናው ቀጥሎ ሰፊ የስራ እድል የሚፈጥር ስለሆነ ዘርፉን ለማሳደግ የፖሊሲ ማሻሻያና የአሰራር ሂደት ለውጥ ለማድረግ እየተሰራ ነው። በአገሪቱ ባለፉት ዓመታት ለተመዘገቡት ለውጦች የኮንስትራክሽን ዘርፉ ሚና የላቀ ቢሆንም በተገቢው መንገድ መመራት ባለመቻሉ  በተፈለገው ደረጃ ለውጥ እያመጣ እንዳልሆነ ዋና ዳይሬከተሩ ገልጸዋል። በዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶችን በማረም የተሻለ ለውጥ ለማምጣት በውጭ አገሮች ተሞክሮ ለውጥ ማምጣት የቻለውን የግንባታ መረጃ ሞዴል ቴክኖሎጂን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል። መረጃ ሞዴሉ የህንጻ ዲዛይኖችን ለመፍጠር፣ የግንባታ ሂደቶችን ለመተንተንና ሌሎች ተዛማጅ ስራዎችን ዘመናዊ በሆነ መንገድ መከወን የሚያስችል የግንባታ መረጃ ሞዴል መሆኑን ገልጸዋል። ''ሞዴሉ የግንባታ ፕሮጀክት ተጀምሮ እስኪያበቃ ድረስ ያለው ሂደት ዘመናዊ አሰራርን በመከተል ዘርፉን ለማሳደግ ያስችላል'' ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ የፕሮጀክቶችን ውጤታማነት በዘመናዊ መንገድ ለመቆጣጠር እንደሚያግዝ አክለዋል። መረጃ ሞዴሉ የግንባታ ጊዜ መዘግየት፣ የዲዛይን ንድፍ ችግሮች፣ የኮንስትራክሽን ወጪ ግነትና ሌሎች ችግሮችን እንደሚቀርፍ የጠቆሙት ኢንጅነር ሞገስ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ተዋናዮች መካከል ጥሩ ተግባቦትን ለመፍጠር እገዛ እንደሚያደርግ አስረድተዋል። በአዲስ አበባና አካባቢው በሚገኙ ፕሮጀክቶች ላይ የመረጃ ሞዴሉ በሙከራ ደረጃ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኢንጂነር ሞገስ ገልጸዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የአሰልጣኞች ስልጠና  የወሰዱ ባለሙያዎችም በቀጣይ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ባለሙያዎች ስልጠናዎችን በመስጠት በዘርፉ ያለውን የባለሙያ እጥረት ለመቅረፍ እንደሚሰራ አክለዋል። የቴክኖሎጂውን ጽንሰ ሃሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም ያስተዋወቁት ፕሮፌሰር ቻርለስ ኤም ኢስትማን ሲሆኑ ለመጀመሪያ ጊዜ በአሜሪካ ጥቅም ላይ ውሏል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም