ጂ አይ ጂ ጋርመንት ሸሚዝና ቲሸርት ማምረቱን አቋርጦ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ማምረት ላይ ተሰማርቷል - ኢዜአ አማርኛ
ጂ አይ ጂ ጋርመንት ሸሚዝና ቲሸርት ማምረቱን አቋርጦ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ማምረት ላይ ተሰማርቷል

አዲስ አበባ ግንቦት 5/2012 (ኢዜአ) የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን ለመከላከል ሲባል ጂ አይ ጂ ጋርሜንት ሸሚዝና ቲሸርት የማምረት ስራውን ለጊዜው በማቋረጥ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ማምረት ላይ መሰማራቱን ገለጸ።
በፋብሪካው ጉብኝት ያደረገው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የግል ባለሀብቶች፣ ወጣቶች እና ሌሎች ለሚያደርጉትን ድጋፍ አመስግኖ ድጋፋቸው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።
በጉብኝቱ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ ኢንጅነር እንዳወቅ አብጤና የጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሃንስ ጫላን ጨምሮ ሌሎች የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ጂ አይ ጂ ጋርሜንት ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ውብሸት እንደገለጹት፤ ድርጅቱ ለወቅታዊ ችግር ምላሽ ለመስጠት የምርት አቅጣጫውን ቀይሯል።
በዚህም ሸሚዝና ቲሸርት የማምረት ስራውን አቋርጦ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ወደማምረት ተግባር መሸጋገሩን ገልጸዋል።
ድርጅቱ በቀን ከ15 እስከ 20 ሺህ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ እያመረተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ማስኮቹ እየታጠቡ በቋሚነት አገልግሎት መስጠት የሚችሉ መሆናቸውን ገልጸው፤ በቀጣይ የማምረት አቅሙን በማሳደግ ተጨማሪ የማምረት ዕቅድ መኖሩን ጠቁመዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ ኢንጅነር እንዳወቅ አብጤ ''የድርጅቱ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ሲባል ሌላ ምርት ትቶ ወደ ማስክ ማምረት ስራ መግባቱ የሚበረታታ ነው'' ብለዋል።
የውጭ ምንዛሬን ከማስቀረት አኳያ ትልቅ አስተዋዕጾ እንደሚኖረውም ገልጸዋል።
የግሉ ዘርፍ መንግስት የኮሮናቫይረስን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመዋል።
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት የተነሳ የገበያ መቀዛቀዝ ያጋጠማቸው ፋብሪካዎች ወቅቱ የሚፈልገውን ምርት በማምረት መስራታቸው ለአገራዊ ኢኮኖሚው አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
የከተማዋ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሃንስ ጫላ በበኩላቸው በሽታው ከተከሰተ ጀምሮ የመከላከል ስራ በተቀናጀ ሁኔታ ሲካሄድ መቆየቱን ጠቅሰው፤ ''ከበሽታው ጋር ተመሳሳይ ምልክት የሚያሳዩ ሰዎችን ምርመራ እንዲካሄድላቸው የቤት ለቤት ክትትል እየተደረገ ነው'' ብለዋል።
በአስሩም ክፍለ ከተማ ለይቶ ማቆያ የተቋቋመ ሲሆን ከዚህ በፊት ከተደረገው በተጨማሪ ከበሽታው ጋር ተመሳሳይ ምልክት የሚያሳዩ ሰዎችን በመከታተል ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ እንደሚደረግ ተናግረዋል።