ቀጥታ፡

የወላይታ ሶዶ ሪፈራል ሆስፒታል የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ጀመረ

ሶዶ ግንቦት 5 /2012 (ኢዜአ) የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል  የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ስራ ዛሬ ጀመረ።

የምርመራው ስራው በተጀመረበት ወቅት የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊና የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባል አቶ አቅናው ካውዛ  እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው የቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።

ዩኒቨርሲቲው የግንዛቤ ማጎልበቻ ስልጠና ከመስጠት ባለፈ የንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘር በማምረት ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

የምርመራ ማዕከል ከዚህ ቀደም በሃዋሳ ከተማ ብቻ እንደነበር ጠቅሰው አሁን የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ሪፌራል ሆስፒታል መምርመራ ጀመሩ ከዚህ በፊት የነበረውን ከፍተኛ የስራ ጫና እና የህብረተሰቡን ስጋት ለመቀነስ እንደሚረዳ አመልክተዋል፡፡


የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ በበኩላቸው የኮሮና ቫይረስን ጨምሮ 96 ናሙናዎችን ለመመርመር የሚያስችል "Real time PCR " የተባለ ማሽን ከዛሬ ጀምሮ ወደ ስራ መገባቱን  አስታውቀዋል።

የኮሮ ቫይረስ ምርመራው ከወላይታ ዞን ባለፈ  ለአጎራባች አካባቢዎችም ጭምር አገልግሎት እንደሚሰጥ ነው የተገለጸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም