ቀጥታ፡

የዲላ ዩኒቨርሲቲ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም ዙሪያ ከፍትህ አካላት ጋር እየሰራ ነው

ዲላ/ወልድያ/ ግንቦት 4/2012 (ኢዜአ )የዲላ ዩኒቨርሲቲ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም ላይ የሚስተዋሉ የግንዛቤ ክፍቶቶችን ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን ሲገልፅ በወልዲያ ከተማ የሚታየው ከልክ ያለፈ መዘናጋት ለማስተካከል ደግሞ እርምጃ ይወሰዳል ተባለ ። 

በዲላ ዩኒቨርሲቲ የህግ ኮሌጅ ዲን መምህር ቶሎሳ በዳዳ ለኢዜአ እንዳሉት ከጌዴኦና አጎራባች የኦሮሚያ ወረዳ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዙሪያ የፍትህ አካላት ያላቸው ግንዛቤ ለማጎልበት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው በአዋጁና ድንጋጌዎች ዙሪያ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት አዋጁን ከማክበርና ከማስከበር አንጻር ክፍተት መኖሩን እንዳረጋገጡ ጠቁመዋል።

ይህን መሰረት በማድረግም ለፖሊስ አመራሮች ፣ ለአቃቤ ህግ ባለሙያዎችና ለሀይማኖት አባቶች በአዋጁ ድንጋጌና መመሪያዎች ዙሪያ የግንዛቤ ማጎልበቻ ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል።

ከአዋጁ ባሻገር የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ወረርሽኙን በመከላከል ረገድ ሊኖራቸው ስለሚገባ ሚናም በጤና ባለሙያዎች የግንዛቤ ማሰጨበጫ ሥልጠና መሰጠቱን ዲኑ ጨምረው ገልጸዋል።

የግንዛቤ ስልጠናውን ካገኙት መካከል የዲላ ከተማ ከንቲባ አቶ ትግሉ በቀለ እንደገለፁት የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እየጨመረ ከሄደ አዋጁ በሚፈቅደው መሰረት ወደ ማስፈጸም ስራ ለመግባት ዩኒቨርሲቲው የሰጣቸው ስልጠና ትልቅ እገዛ ያደርገል ብለዋል።

የሚታዩ መዘናጋቶችንና አዋጁን ያለማክበር ሁኔታ በመቅረፍ ከኮሮና ጉዳት ለመዳን አስፈጻሚው አካል በተሟላ ዕውቀት ታግዞ እንዲሰራ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

በመድረኩ ከሁሉም መዋቅሮች የተውጣጡ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠርና ለመከላከል የተቋቋሙ የግብረ ኃይል አባላት፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሆቴል ባለቤቶች፣ የግል ክሊኒክና የባንክ ሥራ አስኪያጆች ተሳትፈዋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ በወልዲያ ከተማ የኮሮና ቫይረስን በመከላከሉ ሒደት  በህብረተሰቡ ዘንድ የሚስተዋለውን ከልክ ያለፈ መዘናጋት ለማስተካከል ጠበቅ ያለ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ የከተማው ግብረ ሃይል አስታወቋል ።

የግብረ ሃይሉ ሰብሳቢ አቶ መህመድ ያሲን ለኢዜአ እንደገለፁት በከተማው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሚገባው ልክ እየተተገበረ አይደለም ብለዋል ።

የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ ባለበት ወቅት ከልክ ያለፈ መዘናጋት መታየቱ አስከፊ ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል የሚል ስጋት አሳድሯል ።

በተለይም ከሌላ አካባቢ የሚመጡ ዜጎች ተገቢውን የጤና ክትትል ሳይደረግላቸው እራሳቸውን ስለሚደብቁ የስጋት መጠኑን ከፍ እንዳደረገው ገልፀዋል ።

መጠጥ፣ ጭፈራ፣ ጫትና ሽሻ ቤቶችም ቀደም ሲል የተላለፉ እገዳዎችን ችላ በማለት ወደ መደበኛ ስራቸው እየተመለሱ በመሆኑ ጠንካራ የህግ ማስክበር ስራ ይሰራል።

አዋጁን ተከትለው የወጡ ድንጋጌዎች በማያከብሩ ግለሰቦችና ተቋማት ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጅት መደረጉንም አቶ መሀመድ ተናግረዋል ።

የከተማው ነዋሪ መምህር ዳንኤል ግርማ በሰጡት አስተያየት በህዝቡ ዘንድ የሚታየው ቸልተኝነት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ።

በመሆኑም መንግስት የዜጎችን ጤንነትና ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል ህግ በሚተላለፉና ለቫይረሱ መስፋፋት ምክንያት በሚሆኑ ሰዎችና ተቋማት ላይ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስጥ ጠይቀዋል ።

አቶ ተስፋየ አሰፋ የተባሉ ሌላው የከተማ ነዋሪ በበኩላቸው ኮሮናን ለመከላከል እየተስተዋለ ያለው መዘናጋት ዋጋ ያስከፍላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ጠቅሰው በጊዜ ሊታረምይገባልብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም