ወረርሽኙ የሚያስከትለውን ቀውስ ለመከላከል ምዕመናን መተባበርና መደማመጥ አለባቸው - አቡነ ማቲያስ (ፓትርያርክ) - ኢዜአ አማርኛ
ወረርሽኙ የሚያስከትለውን ቀውስ ለመከላከል ምዕመናን መተባበርና መደማመጥ አለባቸው - አቡነ ማቲያስ (ፓትርያርክ)
አዲስ አበባ ግንቦት 5/2012 (ኢዜአ) የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ የሚያስከትለውን ቀውስ ለመከላከል ምዕመኑ መተባበርና መደማመጥ እንዳለበት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ አሳሰቡ።
የቤተ ክርስቲያኒቱ 2012 ዓ.ም የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ ዛሬ ተጀምሯል።
በጉባኤው መክፈቻ ወቅት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ እንዳሉት፤ ኢትዮጽያ በተለያየ ችግር ባለችበት ወቅት የተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሀገሪቱን ስጋት ላይ ጥሏል።
''ይህንን ችግር ለመፍታት ምዕመኑ ከአባቶችና ከመንግሥት የሚመጣውን ምክር በአግባቡ በማዳመጥና በመተግበር ችግሩን መከላከል ይገባል'' ብለዋል።
የሐይማኖት አባቶችም ሕዝቡን በጸሎት፣ በማስተማር፣ በማስታረቅና ሕዝብን የማዳን ስራ በመሥራት አገርንና ሕዝብን ከፈተና መታደግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ይህንን ፈተና ማለፍ የሚቻለው ደግሞ በአንድነትና በማስተባበር ሲሆን፤ የሃይማኖት አባቶች እዚህ ላይ አተኩረው ሊሠሩ ይገባል።
''መንግሥትና የፖለቲካ ፓርቲዎች እግዚአብሔርና ታሪክ የጣለባቸውን አደራ በተግባር በማሳየት ሕዝቡን ከዚህ ክፉ በሽታ ለመታደግ መተባበር አለባቸው'' ብለዋል።
ይህ ወቅት ለአገሪቱም ይሁን ለቤተክርስቲያኒቱ ከባድ ፈተና መሆኑን ያነሱት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፤ ''በትናንት አስተሳሰብ ችግሩን መፍታት አይቻልም'' ብለዋል።
ዛሬ የተሰበሰብነው ሊቃነ ጳጳሳት የሕዝብና የእግዚአብሔር እረኞች ሆነን መዕመናኑን በሁለንተናዊ ህይወቱ ከፈተና መታደግ ይገባናልም ሲሉ ቅዱስነታቸው ገልጸዋል።
''በኢኮኖሚና በሰላም እጦት የሚጎዳውን ደሃውን ህብረተሰብ ልንደግፈው ይገባል'' ነው ያሉት።
የዛሬው ምልአተ ጉባኤም በወቅታዊ የአገሪቱና የቤተክርስቲያን ጉዳይ ተወያይቶ ወደ ተጨባጨ ስራ የሚገባ መሆኑን ጠቁመዋል።
ቤተክርስቲያኗና ቅዱስ ሲኖዶስ ሁልጊዜም ከሕዝቡ ጎን የሚቆሙ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።