ቀጥታ፡

በደቡብ ወሎ ዞን 86 ሺህ ችግረኞችን ለመታደግ የሀብት ማሰባሰብ ስራ እየተካሔደ ነው

ደሴ፣  ግንቦት 5/2012 (ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞን የኮሮና ቫይረስ ባስከተለው ተፅእኖ ለችግር የተጋለጡ 86 ሺህ ወገኖች ለመታደግ የሀብት ማሰባሰብ ስራው በተጠናከረ አግባብ እየተካሔደ መሆኑን በዞኑ የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ኃይል አስታወቀ።

በግብረ ኃይሉ የሀብት አሰባሰብ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጀማል መሃመድ ለኢዜአ እንደገለጹት የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ የመከላከል ስራውን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል።

በአገሪቱ ኮሮና የሚቆይበት ጊዜ እየተራዘመ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ አቅመ ደካሞችና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ በሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እያደረሰ ነው።

ይህን መሰረታዊ ችግር ለመቅረፍ የዞኑ ግብረ ሃይል የጀመረውን የሃብት ማባሰብ እንቅስቃሴ አጠናክሮ ለማስቀጠል በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

በተጨማሪም "ቫይረሱ ሙሉ በሙሉ የጠፋ እስኪመስል ድረስ የተስተዋለው መዘናጋት ዋጋ እንዳያስከፍለን ቅስቀሳ በማድረግና ትምህርት በመስጠት ግንዛቤ የመፍጠር ስራ በአዲስ መልክ እያካሄድን እንገኛለን" ብለዋል።

በዞኑ በተካሄደው የዳሰሳ ጥናት መሰረት በኮሮና ስርጭት ምክንያት ከ86 ሺህ በላይ ዜጎች ድጋፍ እንደሚፈልጉ በመረጋገጡ ከ100 ሺህ ኩንታል በላይ የምግብ እህልና 58 ሚሊዮን ብር ጥሬ ገንዘብ ያስፈልጋል።

እስካሁን በተደረገ ሁሉን አቀፍ ጥረትም  22 ሚሊዮን ጥሬ ገንዘብና 2 ሺህ 900 ኩንታል የምግብ እህል ከንግዱ ማሀበረሰብ፣ ከባለሃብቱ፣ ከአርሶ አደሩና ከሌላው ማህበረሰብ ማሰባሰብ መቻሉን ገልጸዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ህብረት ስራ ማህበራት ተጠሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የግብረ ኃይሉ አባል አቶ ኢብራሂም ሀሰን በበኩላቸው በ24ቱም ወረዳዎች የሚገኙ 2 ሺህ 216 ህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች ማህበራዊ ግዴታቸውን እንዲወጡና ያላቸውን እንዲያጋሩ ግንዛቤ ተፈጥሯል ብለዋል።

እስካሁንም ህብረት ስራ ማህበራቱና ዩኒየኖቹ ከ700 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የምግብ እህልና አንድ ሚሊዮን ብር ጥሬ ገንዘብ በማሰባሰብ ገቢ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

በቃሉ ወረዳ ሃርቡ ከተማ በጎ ፈቃድ ስራ የተሰማራው ወጣት ሁሴን ሰይድ እንዳለው በማህበር ተደራጅተን ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር፣ እጅ በማስታጠብና በገቢ ማሰባሰብ ስራ እየተሳተፍን እንገኛለን ብሏል ።

መጀመሪያ አካባቢ የነበረው የህብረተሰቡ መነቃቃት ከፍተኛ እንደነበር ጠቁሞ አሁን ላይ ግን ቫይረሱ የጠፋ ይመስል እየተቀዛቀዘ በመምጣቱ  በአዲስ መልኩ ቅስቀሳና የግንዛቤ ፈጠራ ስራ በዚህ ሳምንት ጀምረናል የሚል አስተያየት ሰጥቷል ፡፡

በደቡብ ወሎ ዞን ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከ20 ሺህ በላይ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች መሰማራታቸውን ከዞኑ ግብረ ሃይል የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም