ህብረቱ በአንበጣ መንጋ ሰብላቸው ለወደመባቸው 3 ሺ 150 አርሶ አደሮች ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ህብረቱ በአንበጣ መንጋ ሰብላቸው ለወደመባቸው 3 ሺ 150 አርሶ አደሮች ድጋፍ አደረገ
ዲላ ፣ ግንቦት 5/2012 ( ኢዜአ )የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት በአንበጣ መንጋ ሰብላቸው ለወደመባቸው 3 ሺ 150 አርሶ አደሮች ድጋፍ አደረገ።
በህብረቱ የሰላምና አቅም ግንባታ ዳይሬክተር አቶ ደቻሳ ሂርዻ እንደገለፁት በምዕራብ ጉጂ ዞን አባያ ወረዳ በአንበጣ መንጋ በእርሻቸው ላይ ጉዳት ለደረሰባቸው አርሶ አደሮች ትናንት ለአንድ ወር የሚሆን ቀለብ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል ።
በወረዳው የአንበጣ መንጋ ጉዳት ካደረሰባቸው አርሶ አደሮች መካከል ለከፋ ችግር ለተጋለጡ 3 ሺህ 150 አባና እማወራዎች በነብስ ወከፍ 25 ኪሎ ግራም ዱቄትና ማጣፈጫ መከፋፈሉን ጠቅሰዋል።
ለዚሁ ድጋፍ ህብረቱ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን ጠቁመዋል።
በወረዳው በ20 ቀበሌዎች ደጋግሞ የተከሰተው የበረሃ አንበጣ መንጋ በእርሻ ላይ ባደረሰው ጉዳት ከ7 ሺህ የሚልቁ አባወራዎች ና እማወራዎችን ለችግር ዳርጓል ያሉት ደግሞ የአባያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አየለ ደንባ ናቸው።
ወረዳው የደረሰውን ጉዳት ለመቀነስ አርሶ አደሩ በአጭር ጊዜ የሚደርሱ ሰብሎችን እንዲያለማ የግብዓት ስርጭት ቢያደርግም የኮሮና ቫይረስ እንዲሁም የኮሌራ ወረርሽኝ በአካባቢው መከሰቱ ችግሩን እጥፍ ድርብ እንዳደረገው ተናግረዋል ።
በአጭር ጊዜ የሚደርሱ ሰብሎች ለምርት እስከሚደርሱ ድረስ የአርሶ አደሩ የምግብ ዋስትና ችግርን በመቅረፉ ረገድ ህብረቱ ያደረገው አስተዋፅኦ የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል አርሶ አደር ትግስቱ አሬሪ በሰጡት አስተያየት በወረዳው በተከሰተው የአንበጣ መንጋ በአንድ ሄክታር ማሳቸው ላይ የነበረው የበቆሎ ቡቃያ ሙሉ በሙሉ የወደመ ሲሆን በፍራፍሬ ተክሎች ላይም ጉዳት አድርሷል።
ምንም እንኳን ችግሩን ለመቋቋም በአጭር ጊዜ የሚደርሱ ጎመን ፣ ስኳር ድንችና ቦሌቄ የተከሉ ቢሆንም ምርቶቹ እስከሚደርሱ ድረስ ለችግር መዳረጋቸውን ተናግረዋል።
ይህንንም በመረዳት ህብረቱ የምግብ ድጋፍ ማድረጉ ጊዜያዊ ችግሩን የሚቀርፍ መሆኑን አንስተው ለተደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።
የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ካላት መንፈሳዊ ተልዕኮ ጎን ለጎን በሰላም ግንባታ ፣ በመልካም አስተዳደርና በሰብዓዊ ድጋፍ የተለያዩ ተግባራት በማከናወን ላይ መሆኗን የህብረቱ ፕሬዝዳንት መጋቢ ፃድቁ አብዶ ገልፀዋል ።
በተለይ በአካባቢው የነበረውን የሰላም መደፍረስ በዘላቂነት ለመፍታት በእርቅና በይቅርታ ዙሪያ የተለያዩ ትምህርቶችን ከመስጠት ጎን ለጎን የበረሃ አንበጣና የኮሮና ቫይረስ እያደረሰ ያለውን ጫና ለማቃለል በማሰብ ድጋፍ መደረጉን አስረድተዋል ።
ህብረተሰቡ እራሱን በመጠበቅና እርስ በራሱ በመረዳዳት እንደ ሀገር የተጋረጠውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝና የአንበጣ መንጋን ለማሸነፍ የበኩሉን አስተዋፅኦ ማበርከት እንዳለበት አስገንዝበዋል።