ቀጥታ፡

መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ለአምስት መቶ አካል ጉዳተኞችና አቅመ ደካሞች ድጋፍ አደረገ

ጎባ (ኢዜአ) ግንቦት 5/2012 ዓ.ም የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ አምስት መቶ አካል ጉዳተኞችና አቅመ ደካሞች የምግብ፣ ዘይትና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ፡፡

ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን ማህበረሰብ የኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚያግዙ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል ።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አህመድ ከሊል እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው የማህበረሰቡን የኮሮና ተጋላጭነት ለመቀነስ ቅድሚያ ሰጥቶ ካከናወናቸው የመከላከል ተግባራት መካከል የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ዋነኛው ነው፡፡

በዚህም ይበልጥ ተጋላጭ ይሆናሉ ተብሎ በተገመቱ የባሌና ምዕራብ አርሲ ዞኖች የገጠር ወረዳዎች ውስጥ ዘላቂ የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በዩኒቨርሲቲው የጤና ባለሙያዎች አማካኝነት መሰጠቱንም ተናግረዋል።

ዶክተር አህመድ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው የግንዛቤ ተግባራትን ከማከናወኑ በተጓዳኝ ለዩኒቨርሲቲው ጤና ባለሙያዎች ሳኒታይዘር የማዘጋጀትና ከ250 የሚበልጡ ክፍሎችን ለህሙማን ለይቶ ማቆያ ማዕከል በቁሳቁስ የማሟላት ስራ እየተሰሩ ከሚገኙ አበይት ተግባራት መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን ማህበረሰብ የማገልገል ኃላፊነት አለበት ያሉት ዶክተር አህመድ የህዝቡን ችግር ለማቃለል በማሰብም በባሌ ፣ ሮቤና ጎባ ከተሞች ውስጥ ለሚገኙ 500 ለሚሆኑ አካል ጉዳተኞችና አቅመ ደካሞች የምግብ፣ ዘይትና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ ማደረጉን ገልፀዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በከተማ አስተዳደሩ ተለይተው ለቀረቡለት ወገኖች ያደረገው ድጋፍ ከ543 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ሲሆን በቀጣይም አቅሙ በፈቀደ መጠን ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል ፡፡

ድጋፍ ከተደረጋላቸው የሮቤ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ መሐመድ አህመድ  በሰጡት አስተያየት የቤተሰባቸውን የወር የምግብ ቀለብ በማግኘታቸው ዩኒቨርሲቲውን አመስግነዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የጀመረውን በጎ ተግባር ሌሎችም አጠናክረው ሊቀጥሉበት ይገባል ያሉት ደግሞ አቶ ሀሰን በከር የተባሉ አካል ጉዳተኛ ናቸው።

በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የሮቤ ከተማ ከንቲባና የከተማዋ የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ኃይል የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አብዱልጀሊል አብዱሮ በበኩላቸው በአስተዳደሩ እስካሁን ከጥሬ ገንዘብ ውጭ በዓይነት 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የምግብ እህል በመጋዘን መከማቸቱን ገልፀዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በከተማዋ ለሚገኙ አቅመ ደካሞችና አካል ጉዳተኞች ላደረገው ድጋፍም አመስግኗል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም