በኦሮሚያ በንግድ እና ፋብሪካዎች አካባቢ ኮሮናን በመከላከሉ በኩል መዘናጋት ይስተዋላል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ በንግድ እና ፋብሪካዎች አካባቢ ኮሮናን በመከላከሉ በኩል መዘናጋት ይስተዋላል
አዳማ፣ ግንቦት 4/2012 (ኢዜአ ) የኦሮሚያ ክልል የኮሮና በሽታ መከላከል ግብረ ኃይል በንግድ ተቋማት፣ ፋብሪካዎችና የገበያ አካባቢ ባደረገው ምልከታ ኮሮናን በመከላከሉ በኩል መዘናጋት እንደሚስተዋል ገለጸ።
የክልሉ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ያካተተው ግብረ ኃይል ምልከታውን ያደረገው ዛሬ በአዳማ ከተማ የንግድ ተቋማት፣ ገበያ እና ፋብሪካዎች አካባቢ ነው።
የግብረ ኃይሉ አባልና የክልሉ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልቃድር ሁሴን እንደገለጹት በከተማው ባደረጉት ምልከታ መዘነጋትና የጥንቃቄ ጉድለት መኖሩን አስተውለዋል።
የተጨናነቀ የገበያ ቦታዎች ወደ አራት ቦታ በማካፈል የበሽታውን ሥርጭት ለመቀነስ የተደረገው ጥረት አበረታችና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው ብለዋል።
ሆኖም አብዛኛው ሻጭና ሸማች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ በገበያ ቦታ ያለመጠቀም፣ የትራንስፖርት እንቅስቃሴም ላይ፣ በፋብሪካ ሠራተኞች አካባቢ መዘነጋትና የጥንቃቄ ችግር መኖሩን በምልከታቸው ማስተዋላቸውን አቶ አብዱልቃድር ገልጸዋል።
"በከተማው የሚታየው መዘነጋት ዋጋ ያስከፍላል" ያሉት ዳይሬክተሩ አስተዳደሩም ሆነ ተቋማቱ ፈጥነው የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
የአዳማ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ደሜ በበኩላቸው የቫይረሱን ሥርጭት ለመከላከል እየተወሰዱ ያሉት እርምጃዎች ይበልጥ ተጠናከረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
"በግብረ ኃይሉ የመስክ ምልከታ የተለዩ ችግሮች ፈጣን መፍትሔ ለመስጠት እንሠራለን" ብለዋል፡፡
የተሰጣቸውን መመሪያ በመጣስ አለአግባብ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉና ምርትን በመደበቅ ሰው ሰራሽ እጥረት በገበያ ላይ እንዲፈጠር ምክንያት ናቸው በተባሉት ከ600 በላይ ነጋዴዎችና የንግድ ተቋማት የንግድ ፈቃድ ከመነጠቅ እስከ ማሸግ የሚደርስ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።
የችግሩ ግንባር ቀደም ተዋናይ የሆኑት ለፍርድ ቤት እንዲቀርቡ መደረጉንም ጠቅሰዋል፡፡
የአትክልትና ፍራፍሬ መገበያያ የነበሩ ሥፍራዎች ወደ ሌላ አካባቢ በማከፋፈል ኅብረተሰቡ ርቀቱን ጠብቆ እንዲገበያይ ጥረት መደረጉንም አመልክተዋል፡፡