የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና አገራት ቀውሶችን መቋቋም የሚያስችል አቅም እንዲገነቡ ያስችላቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና አገራት ቀውሶችን መቋቋም የሚያስችል አቅም እንዲገነቡ ያስችላቸዋል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4/2012 (ኢዜአ) የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና አባል አገራት በረጅም ጊዜ ቀውሶችን መቋቋም የሚያስችል አቅም መገንባት እንዲችሉ ያደርጋል ሲሉ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ቀጠናዊ ትስስርና የንግድ ዳይሬክተር ስቴፈን ካሪንጊ አስታወቁ።
የንግድ ቀጠናው የአፍሪካ ኢኮኖሚ በኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ምክንያት ከደረሰበት ጉዳት እንዲያገግም የሚያግዝ ነውም ብለዋል።
የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ቀጠናዊ ትስስር የንግድ ዳይሬክተር እና የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ስቴፈን ካሪንጊ ትናንት ከጋዜጠኞች ጋር በኢንተርኔት (ዌቢናር) ውይይት ማካሄዳቸውን ኮሚሽኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ለጋዜጠኞቹ በሰጡት ማብራሪያ፤ በአፍሪካ አገራት መካከል ያለው የንግድ ትስስር የአገራትን የኢኮኖሚ አማራጮች የሚፈጥር ነው።
የንግድ ትስስሩን ማሳደግ ለስራ ፈጠራ፣ ለውጭ ምንዛሬ፣ ለኢንዱስትሪ ልማትና የኢኮኖሚ እድገት የማነቃቂያ ማዕቀፍ እንደሚሆንም ገልጸዋል።
የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ጨምሮ ሌሎች ስምምነቶችና የትብብር ማዕቀፎችን አፍሪካ ተግባራዊ ብታደርግ በመድሐኒት ማምረት፣ በግብርና በኢንዲስትሪ ልማት ያቀደቻቸው መርሃ ግብሮች ውጤታማ እንዲሆን ያደርግ ነበር ብለዋል።
የአፍሪካ ኢኮኖሚ ይበልጥ ብዝሃነት ኖሮት ቢሆን በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የሚደርስበት ጉዳት ዝቅተኛ ይሆን እንደነበረም ነው ሚስ ስቴፈን ያመለከቱት።
ነገር ግን "ኮቪድ-19 የአፍሪካ አገራት ነገሮችን መላመድና ለፍላጎቶች ተገቢውን ምላሽ መስጠት የምትችልበትን ሁኔታ ያረጋገጠ ነው " ብለዋል ዳይሬክተሩ።
በደቡብ አፍሪካ ለግብርናና ለማዕድን ሰራተኞች ብቻ የአፍና ፊት መሸፈኛ ጭምብል የሚያመርተው "ዩ-ማስክ" ኩባንያ በኮቪድ-19 መከላከያ ጭምብል ወደ ማምረት መዞሩን ጠቅሰዋል።
የናይጄሪያው ብሔራዊ የሳይንስና የምህንድስና መሰረተልማት ኤጀንሲ አገር በቀል የሆኑ የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያዎች (ቬንትሌተሮች) ማምረት መጀመሩንም አውስተዋል።
ሰኔ 24 ቀን 2012 ዓ.ም በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ማዕቀፍ ስር በአገራት መካከል ንግድ ለመጀመር ቀነ ቀጠሮ ተይዞ ነበር።
ነገር ግን በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ንግድ የሚጀመርበት ቀን ወደ ታህሳስ 2012 ዓ.ም መራዘሙ የሚታወስ ነው።
ቀኑ መራዘሙ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና በ21ኛው ክፍለ ዘመን ካሉ አዳዲስ እውነታዎችና አደጋዎችን ባገናዘበ መልኩ ማሻሻያዎችን አድርጎ ንግድን ለማካሄድ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ አዳዲስ ሀሳቦች እንዲፈጠሩ የእድል በር እንደሚከፍቱ ነው ስቴፈን ካሪንጊ ያስታወቁት።
በዚህም አፍሪካ ወደፊት ኮሮናቫይረስ ለማስወገድ፣ የአየር ንብረት ተጽእኖና ወደ ፊት የሚገጥሟትን ቀውሶች ለመቋቋም የሚችሉበት ሁኔታ ላይ መድረስ እንደሚችሉ አመልክተዋል።
የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ህልምና ተግባራዊነት በማስቀጠል የአፍሪካ አገራት የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና አገራት ቀውሶችን መቋቋም የሚያስችል አቅም እንዲገነቡ ያስችላቸዋል ብለዋል።
የአፍሪካ የንግድ ፖሊሲ ማዕከል አስተባባሪ ሚስ ዴቪድ ሉክ አፍሪካ የንግድ ሰንሰለት ምንጮቿን ማስፋት እንደሚገባት ገልጸዋል።
ኮቪድ-19 የንግድ ሰንሰለቱ አማራጭ ያላደገ መሆኑን ያሳየና አፍሪካ የንግድ ሰንሰለት ምንጮቿን ማስፋቷ አፍሪካ ከያዘችው በኢንዱስትሪ የማደግ አጀንዳ ጋር የሚጣጣም ነው ብለዋል።
አሁን ያሉ የልማት ማዕቀፎችን እንዴት በቀውሶች አማካኝነት የሚፈጠሩ አዳዲስ እድሎች ጋር አላምዶ መተግበር ይቻላል? በሚለው ጉዳይ ላይ አዲስ አስተሳሰብ ማምጣት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ቀጠናዊ ትስስርና የንግድ ዳይሬክተር ሚስ ስቴፈን ካሪንጊ ኮቪድ-19 ለአፍሪካ ህብረት አባል አገራት የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች ጠቀሜታን ያሳየ ነው ብለዋል።
ኢ-ኮሜርስን ጨምሮ በሌሎች ቴክኖሎጂዎች አማካኝነት አባል አገራቱ የተለያዩ ስምምነቶች መፈራረም እንደሚችሉና ይህም ከአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት ምዕራፍ ሁለት ስምምነቶች ጋር የቅርብ ትስስር እንዳለውም ገልጸዋል።
ጋዜጠኞች ሁልጊዜ የአፍሪካ አገራት መሪዎችን በአህጉሪቱ እቅዶች የገቡትን ቃል በየጊዜው ማስታወስ እንደሚጠበቅባቸው በዚህም ስምምነት ብቻ ሆነው እንዳይቀሩና እንዲተገብሩ ማድረግ እንደሚገባም ጠቅሰዋል።
የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ከ"አፍሪካ ውመን ኢን ሚዲያ ኔትወርክ" ጋር በመተባበር በኢንተርኔት አማካኝነት የተደረገው ጉባኤ (ዌቢናር) ጋር በትብብር የተዘጋጀ ነው።
ጉባኤው በቅርቡ ኮሚሽኑ "ኮቪድ በአፍሪካ ህይወትና ኢኮኖሚን መጠበቅ" በሚል ባወጣው ሪፖርት ላይ ግንዛቤ የመፍጠር አካል እንደሆነ የኮሚሽኑ መረጃ ያመለክታል።
ሰኔ 30 ቀን 2012 ዓ.ም በኒጀር ርዕሰ መዲና ኒያሚ በተካሄደው 12ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ልዩ መደበኛ ስብሰባ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስራ እንዲጀምር መወሰኑ የሚታወስ ነው።
በስብሰባው ላይ ከኤርትራ ውጪ 54 የአፍሪካ አገራት ስምምነቱን የፈረሙ ሲሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ 28 አገራት ስምምነቱን አጽድቀውታል።
የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት ወደ ተግባር ለማስገባት በ22 አገራት በህግ አውጪው ምክር ቤት መጽደቅ እንዳለበት የተቀመጠ ሲሆን በዚሁ መሰረት ስምምነቱ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።
አጋርነቱ እ.አ.አ በ2022 በአፍሪካ አገሮች መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ በ52 በመቶ በማሳደግ በመካከላቸው ያለውን የሸቀጦች የንግድ ታሪፍ በ90 በመቶ ያስቀራልም ተብሎለታል።
አገልግሎቶችን ነጻ በማድረግና እርስ በርስ የንግድ ልውውጥ ሂደት የሚታዩ ሌሎች መሰናክሎችን በማስወገድ በተለይም በድንበር ላይ የሚደረገውን አሰልቺ ቁጥጥር በማሳጠር አገራቱን ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደሆነ ተገልጿል።