የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፎረም ለኮሮናቫይረስ መከላከያ ከ684 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፎረም ለኮሮናቫይረስ መከላከያ ከ684 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፎረም ከተለያዩ አባል ማህበራት ያሰባሰበውን ከ684 ሚሊዮን ብር በላይ ለኮቪድ 19 መከላከያ እንዲውል ድጋፍ አደረገ።
የፎረሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በሰጡት ማብራሪያ ከአባላቶቻቸው የተሰበሰበውን 684 ሚሊዮን 199 ሺህ 943 ብር ግምት ያለው ገንዘብና ቁሳቁስ ለኮቪድ 19 መከላከያ እንዲውል ድጋፍ አድርገናል ብለዋል።
ይህም በኢትዮጵያ ቫይረሱ መከሰቱን ተከትሎ መንግስት ያቀረበውን ጥሪ በመቀበል የተደረገ ምላሽ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፎረም 12 አባላት ያሉት ግብረ ሃይል አቋቁሞ ወደ ስራ የገባ ሲሆን አስካሁንም የግብአትና የገንዘብ ድጋፎችን እያሰባሰበ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ከተለያዩ አባል ማህበራት የተሰበሰበውን የገንዘብና ቁሳቁስ ድጋፍ በዛሬው እለት ለብሄራዊ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አስረክቧል።
ግብረ ሃይሉ ቀደም ሲል ከደሞዝ መዋጮ ያሰባሰበውን ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ለዚሁ ተመሳሳይ ተግባር እንዲውል ለሰላም ሚኒስቴር ማስረከቡ ታውቋል።
የፎረሙ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በበኩላቸው ማህበራቱ ከተቋቋሙለት ዓላማ አኳያ ተግባሩን ማጠናከርና ማስቀጠል ይገባቸዋል ብለዋል።
የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት ከሲቪክ ማህበራት በተጨማሪ ሁሉም ማህበረሰብ ሊያግዝ ይገባልም ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፎረም ከ1 ሺህ 500 በላይ አባል ማህበራት እንዳሉት ታውቋል።