ከሱዳን ድንበር በሚያዋስነው ቋራ ወረዳ የሚካሄደው ህገ ወጥ ንግድ የኮሮና ስጋትን ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
ከሱዳን ድንበር በሚያዋስነው ቋራ ወረዳ የሚካሄደው ህገ ወጥ ንግድ የኮሮና ስጋትን ፈጥሯል
መተማ፤ ግንቦት 4/2012 (ኢዜአ) ከሱዳን ድንበር ጋር በሚያዋስነው በምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ የሚካሄደው የህገ-ወጥ ንግድ እንቅስቃሴ የኮሮና ስጋት እንደፈጠረባቸው በወረዳው አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
የወረዳው ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል በበኩሉ እርምጃ እየወሰድኩ ነው ብሏል።
አቶ አስማማው ግስሜ በቋራ ወረዳ የገለጉ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ በወረዳው በአይሰጋ ቀበሌና በሱዳን ቲሃ አካባቢ ከፍተኛ ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ እንዳለ መታዘባቸውን ገልጸዋል።
በእዚኒህ አካባቢዎች ቁጥጥር የማይደረግባቸው በመሆኑ የኮሮቫይረስ ሊያጠቃን ይችላል የሚል ስጋት እንደፈጠረባቸውም ተናግረዋል፡፡
"ለሚመለከተው አካል ጥቆማ ብንሰጥም እርምጃ ሲወሰድ እያየን አይደለም" ያሉት ነዋሪው የሚመለከተው አካል ትኩረት በመስጠት የህዝብን ደህንነት ሊያስጠብቅ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
በወረዳው የነብስ ገበያ ቁጥር አንድ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ተመስገን አጥቃው በበኩላቸው በቀበሌያቸው በኩል ወደ ሱዳን ከፍተኛ የገቢና ወጭ የኮንትሮባንድ ንግድ ሲካሄድ መመልከታቸውን ይገልጻሉ።
"ዘይት፣ ቀይ ሽንኩርት፣ ጨው፣ ለስላሳ መጠጦች፣ ስኳርና የጦር መሳሪያ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ፤ ነጭ ሽንኩርት፣ ባቄላና የቀንድ ከብት ደግሞ ወደ ሱዳን የሚሄዱ ምርቶች ናቸው" ሲሉም ጠቁመዋል።
ህገ-ወጥ ንግዱ የሃገሪቱን ኢኮኖሚ እየተጎዳ ከመሆኑም በላይ ለኮሮና ቫይረስ እንዳይጋለጡ በስጋት እየኖሩ መሆናቸውን ተናግረው፤ "ለአካባቢው አስተዳደር አቤት በማለት ላይ እንገኛለን" ብለዋል።
የወረዳው የፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባል ረዳት ኢንስፔክተር ዳምጠው ሞላ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ህገ ወጦች በጫካ ተደብቀው በመግባት የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ የሚያደርጉትን ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በተደረገው ጥረትም 24ኩንታል ጨው፣ 67ኩንታል ቀይ ሽንኩርት፣ 37ኩንታል ነጭ ሽንኩርት፣ ሁለት ሞተር ብስክሌትና ዘጠኝ ኩንታል ስኳር በቅርቡ በቁጥጥር ስር መዋሉን ጠቅሰዋል።
ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የገቡ እቃዎችን በቤታቸው ደብቀው የተገኙት አምስት ተጠርጣሪዎችም ምርመራ እየተደረገባቸው ነው ብለዋል።
ህገ ወጥ መሳሪያ ይዘው ሲገቡ የተገኙ ሁለት ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም አመልክተዋል።
ህዝቡም ከፀጥታ አካላት ተሰውረው ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ኮንትሮባንድ የሚነግዱ አካላትን በመጠቆም ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ከሱዳን በሚያዋስኑ አካባቢዎች በልዩ ሁኔታ ጥበቃና ክትትል እንደሚደረግ የአማራ ክልል ሰላምና የህዝብ ደህንነት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሲሳይ ዳምጤ በቅርቡ ለኢዜአ ገልጸዋል።
ኃላፊው በወቅቱ እንዳሉት በምዕራብ ጎንደር ዞን ማቆያ ቦታዎች መደበኛ የሆነ የፀጥታ አካል በዞኑ ሰላምና ደህንነት ዘርፍ በኩል ይመደባል፡፡
በድንበር ጫካን ከለላ አድርገው የሚገቡ ግለሰቦችን ለመያዝና ለመቆጣጠርም በየቀበሌው ለሚገኝ ሚሊሻ ስምሪት በመስጠት ለመከላከል ጥረት እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡
በዞኑ የግብረ-ኃይሉ ሰብሳቢና ዋና አስተዳዳሪ አቶ አደባባይ ሙሉጌታ በተለይም ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የገቡ 3 ሺህ የሚጠጉ ዜጎችን በሙቀት ልኬት እንዲያልፉ መደረጉን አመልክተዋል።
ሆኖም ከድንበር አልፈው ጫካ የሚገቡት ዜጎች መኖራቸውንና እስካሁን በተደረገው የቁጥጥር ስራም 86 ዜጎች ወደ ለይቶ ማቆያ መግባታቸውን ቀደም ሲል ዘግበናል፡፡