ቀጥታ፡

የለኩ ከተማ ተጎጂዎች የመንግስትን ድጋፍ ጠየቁ

ሃዋሳ ሰኔ 28/2010 በሲዳማ ዞን ሸበዲኖ ወረዳ ለኩ ከተማ በሁከትና ግርግር የንግድና የመኖሪያ ቤታቸው የወደመባቸው ነዋሪዎች  ከደረሰባቸው ጉዳት አገግመው ወደ ወትሮ ሥራቸው ለመመለስ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸው  ጠየቁ፡፡ የደኢህዴን ሊቀመንበርና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በከተማው ተፈጥሮ በነበረ ሁከት በቃጠሎ የወደሙ ንብረቶችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡ በከተማው ተወልደው ማደጋቸውን የሚናገሩትና በንግድ ሥራ የተሰማሩት አቶ ሲሳይ በላቸው እንዳሉት ሰኔ 8 እና 9 በከተማዋ ተከስቶ በነበረ ሁከት የንግድና የመኖሪያ ቤቶቻቸው በቃጠሎ ወድመዋል፡፡ ሰርተው ቤተሰቦቻቸውን ያስተዳድሩበትና ለመንግስት ግብር ይከፍሉበት የነበረው ንብረታቸው በሁከትና ግርግሩ መውደሙን ገልጸው ጉዳቱ ለእነሱ ብቻ ሳይሆን ለከተማዋና ለአካባቢው እድገት ጭምር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ሙዲ ኪያር በበኩላቸው የንግዱ ማህበረሰብ ሰርቶ ለመንግስት ግብር የሚከፍልና እያንዳንዱም ከ10 እስከ 15 ሰው የሚያስተዳድር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የደረሰባቸውን ችግር እንዳይናገሩ ዛቻ እየደረሰባቸው መሆኑንና በአካባቢው የፖሊስ መዋቅር አመኔታ እንደሌላቸው የገለጹት አቶ ሙዲ፣ በቀጣይ በሌሎች የጸጥታ አካላት ጥበቃ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡ በከተማው ይህ ችግር ሊከሰት እንደሚችል አመራሩ መረጃ ነበረው ያሉት ደግሞ ሌላው ተጎጂ አቶ አበበ ዘውዴ ናቸው። " ችግር ተከስቶ ጉዳት እንዳይደርስብን ስጋታችንን ስንገልጽ ወረዳውና ከተማው በቂ የፖሊስ ኃይል አለው ስጋት አይግባችሁ፤ ድርጅታችሁን ከፍታችሁ ስሩ  ተብለን ወደ ሥራ በገባንበት ወቅት ዝርፊያና ቃጠሎ ደረሰብን" ብለዋል፡፡ የለኩ ከተማ ከንቲባ አቶ ታረቀኝ ዳሪሞ በበኩላቸው እንዳሉት በወቅቱ ይህን ያህል ጉዳት ይፈጸማል የሚል ስጋት እንዳልነበራቸውና ችግር ቢፈጠር በራስ አቅም እንቋቋማለን በሚል እሳቤ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር አስታውሰዋል። "አደጋው ከፍተኛ መሆኑን ሲታወቅ ድጋፍ ጠይቀን መከላከያና ልዩ ኃይል እንዲገባ አድርገናል" ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የተጎጂ ተወካዮች ባሉበት የወደመውን የንብረት መጠን የሚያጣራ ኮሚቴ መዋቀሩንም ከንቲባው ተናግረዋል። የደኢህዴን ሊቀመንበርና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ከጉብኝቱ በኋላ በተደረገ ውይይቱ እንዳሉት የሲዳማ ህዝብ እንደሌሎቹ የክልሉና የአገሪቱ ህዝቦች ተቻችሎ፣ ተሳስሮና ተከባብሮ የሚኖር ነው፡፡ የወደመውን ንብረት መመለስ እንደማይቻል የጠቆሙት አፈጉባኤዋ በቀጣይ ዘላቂ መፍትሄው ላይ በመረባረብ የተጎዱ ወገኖች ቀደሞ ወደ ነበሩበት ሁኔታ ለመምጣት አተኩሮ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ተጎጂዎችን ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ለመመለስ የክልሉ መንግስት የጀመረው ሥራ እንዳለ ጠቁመው የወረዳውና የዞኑ አመራሮች ህዝቡን በማስተባበር ተጎጂዎችን ለመደገፍና የጠላትነት መንፈስ እንዳይፈጠርባቸው ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም