ቀጥታ፡

"ነርሶች ኮሮናን ለመከላከል ተጋድሎ እያደረጉ ነው፤ ሥራቸውም ምትክ የለውም" ... ዶክተር ሊያ ታደሰ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 4/2012(ኢዜአ) በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ከተከሰተ ጀምሮ "ነርሶች ሥራ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ተጋድሎ እያደረጉ ነው" ሲሉ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ተናገሩ።

በዛሬው ዕለት የሚከበረውን የዓለም ነርሶች ቀን አስመልክቶ የጤና ሚኒስቴሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ከኢትዮጵያ ነርሶች ማኅበር ጋር መግለጫ ሰጥተዋል።

ዶክተር ሊያ እንደገለጹት፤ ያለነርሶች የሚታሰብ ምንም አይነት የጤና አገልግሎት የለም፤ መሪ ቃሉ እንደሚለው "ነርሶች ዓለምን ወደ ጤና የሚያደርሱ መሪዎች ናቸው"።

"በዚህ ዘመን ኮቪድ 19 ደግሞ ሥራቸውን ከባድ፤ አስተዋጿቸውንም ምትክ የሌለው አድርጎታል" ብለዋል።

ቫይረሱ በኢትዮጵያ ከተከሰተ ጀምሮ በአገሪቱ የሚገኙ ነርሶች "ሥራ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ተጋድሎ እያደረጉ ነው" ሲሉም ተናግረዋል።

በተለያዩ የጤና ተቋማትም የሰውን ህይወት ለማትረፍ የራሳቸውን ጤናና ህይወት በመሰዋት እያገለገሉ ይገኛሉ ብለዋል።

ነርሶች ቤተሰቦቻቸውንና ልጆቻቸውን አስቀምጠው የሌሎችን ልጆችና ቤተሰብ ለማከም መስዋዕትነት እንደሚከፍሉም ተናግረዋል።

ነርሶች የሚያክሟቸውን እንደ ራሳቸው የሚያዩና በቅንነት ሥራቸውን የሚከውኑ ባለሙያዎች መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

ያም ሆኖ የታካሚዎች ደህንነትና ጤንነት ነርሶች በሚሰጡት አገልግሎት ጥራት ላይ እንደሚወሰን ገልጸው፤ ነርሶች ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠታቸውን እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ነርሶች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ታፈሰ በቀለ፤ በአሁኑ ወቅት የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ነርሶች ግንባር ቀደም ተሰላፊ ባለሙያዎች ናቸው ብለዋል።

በኢትዮጵያም ኮሮናቫይረስ ከገባ ጀምሮ የአገሪቱ ነርሶች የሙያ ሃላፊነታቸውን በብቃት እየተወጡ መሆኖቸውን ነው የገለጹት።

ኅብረተሰቡም ነርሶች የሚሰጡትን አገልግሎት ከግምት በማስገባት ክብር ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል።

የማኅበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት ሲስተር ረዲ ዘገየም ነርሶች የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለማሸነፍ ከፍተኛ ትግል እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ አጋጣሚ ሁሉም ነርሶች ሙያዊ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት በትጋታቸው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

ይሁን እንጂ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ነርሶች ብቻ ሳይሆን የሁሉም እገዛና ትብብር እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት።

በተለይም ኅብረተሰቡ ከጤና ባሙያዎችና ከመንግሥት የሚሰጡትን መመሪያዎች ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበትም አሳስበዋል።

በተያዘው የፈረንጆች ዓመት በዓለም ጤና ድርጅት እለቱ "የነርሶችና የአዋላጅ ነርሶች ዓመት" ተብሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተከበረ ይገኛል።

የዘንድሮ የዓለም የነርሶች ቀን ዘመናዊ የነርስ አገልግሎት ያስጀመረችው ፍሎረንስ ናይቲንጋሌ (ባለፋኖሷ እመቤት) 200ኛ የልደት በዓል ጋር አብሮ ታስቦ እየዋለ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም