ቀጥታ፡

በትግራይ ደቡባዊ ዞን 3ሺህ 370 ለሚሆኑ የተቸገሩ ወገኖች የምግብ ድጋፍ ተደረገ

ማይጨው ግንቦት 03/2012(ኢዜአ ) በትግራይ ደቡባዊ ዞን ለሚገኙና የምግብ እህል እጥረት ላለባቸው ሦስት ሺህ 370 ወገኖች ድጋፍ ተደረገ።

ድጋፉ የዳቦ ዱቄት ሲሆን  በማስተባበር ያመቻቸውም  "ህብረት ለራያ ልማት ማህበር"  ነው።

የማህበሩ ሊቀመንበር  ዶክተር አከዛ አውዓሎም ድጋፉ  እንዳሉት የዳቦ ዱቄቱን   ለእያንዳንዱ ሰው  10 ኪሎ ግራም  እንዲደርሰው ተደርጓል።

"የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ  የፈጠረው ጫና መከላከል የሚቻለው የምግብ እጥረት ላጋጠማቸው ወገኖች ድጋፍ በማድረግ ጭምር ነው "ብለዋል።

ለማገዝም ድጋፉን በዞኑ ለሚገኙ ሦስት ሺህ 370 የተቸገሩ ወገኖች ማከፋፈላቸውን አሰረድተዋል።

የዳቦ  ዱቄቱ በሀገር ውስጥና  ሰሜን አሜሪካ ከሚኖሩ የራያ ተወላጆች በሰጡት የገንዘብ ድጋፍ   የተገዛ መሆኑን አመልክተው እገዛው በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። 

በዞኑ የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል የጤና ንኡስ ኮሜቴ አስተባባሪ አቶ አብርሃ ደሳለው በበኩላቸው በማህበሩ አማካኝነት የተገኘው ድጋፉ  በምግብ እጥረት ምክንያት የተቸገሩ ወገኖች የከፋ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ያግዛል ብለዋል።

የማይጨው ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ መብራት በርሄ ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል አንዷ ሲሆኑ በሰጡት አስተያየትም በድጋፉ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የመቀሌ  ታክሲ ማህበር አባላት ኮሮናን ለመከላከል እንዲያግዝ  ከ120 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ አድርገዋል።

የማህበሩ  አስተባበሪ አቶ ካልአዩ አብረሀ  የገንዘብ ድጋፉ የተሰበሰበው ከአባላት መሆኑን ተናግረዋል።

ገንዘቡንም ለክልሉ ጤና ቢሮና በኢትዮጰያ ቀይ መስቀል ማህበር የትግራይ ቅርንጫፍ አስረክበዋል።

ሪፖርተሮች  ይብራህ አምባዬ እና አረጋዊ መዝገበ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም