በጋሞ ዞን ወረርሽኙን ለመከላከል 25 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ በዓይነት ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በጋሞ ዞን ወረርሽኙን ለመከላከል 25 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ በዓይነት ተሰበሰበ
አርባ ምንጭ ግንቦት 3/2012(ኢዜአ) ... በጋሞ ዞን ኮሮናን ለመከላከል የሚረዳ 25 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ በዓይነት መሰብሰቡን የዞኑ ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አስታወቀ።
የአርባ ምንጭ መምህራን ኮሌጅ ያመረታቸውን 1 ሺህ 200 ብልቃጥ ሳኒታይዘር ዛሬ ለዞኑ ሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴ አስረክቧል።
በዚህ ወቅት በግብረ ኃይሉ የሀብት አሰባሰብና በጎ አድራጎት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አሸናፊ ናና እንደገለጹት ባለፉት ሁለት ወራት በተደረገው ሃብት የማሰባሰብ ስራ የተሰበሰበው ድጋፍ 17 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ እና 8 ሚሊዮን ብር የሚገመት ደግሞ በዓይነት ነው።
በጋሞ ዞን 14 ወረዳዎችና አራት የከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ ነጋዴዎች፣ የመንግስት ተቋማትና ሠራተኞች፣ ማህበራትና መንግታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በድጋፉ ተሳትፈዋል።
የአርባ ምንጭ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ዲን አቶ አያሌው አበራ በበኩላቸው ኮሌጁ በደቡብ ክልል የሳይንስ ላባራቶሪ ባለሙያዎችን በማፍራት ግንባር ቀደም መሆኑን ገልጸዋል።
ኮሌጁ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመግታት የሚያግዝ ሳኒታይዘር በማምረት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በተቋማቸው የተመረተው 1 ሺህ 200 ብልቃጥ ሳኒታይዘር ለዞኑ ሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ዛሬ አስረክቧል።