የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ በአግባቡ እየተጠቀሙ ነው - ኮርፖሬሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ በአግባቡ እየተጠቀሙ ነው - ኮርፖሬሽኑ
አዲስ አበባ ግንቦት 3/2012 (ኢዜአ) የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ በአግባቡ እየተጠቀሙ መሆኑን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ገለፀ።
በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሥርጭትን ለመቀነስ በትራንስፖርት ውስጥ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ማድረግ አስገዳጅ እንዲሆኑ መደረጉ ይታወሳል።
ከዚህ አንፃር በባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ተሳፋሪዎች የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማስክ አጠቃቀማቸውን በተመለከተ ኢዜአ ከኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ስንታየሁ ወልደሚካኤል ጋር ቆይታ አድርጓል።
የኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ስንታየሁ ወልደሚካኤል የኮሮናቫይረስ በኢትዮጵያ ከተገኘበት ዕለት አንስቶ በሽታው በትራንስፖርት እንዳይስፋፋ የተለያዩ ጥንቃቄዎችን ሲወስድ መቆየቱን ተናግረዋል።
አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መሰረት አድርጎ በወጡ ደንብና መመሪያዎችን የባቡር ትራንስፖርትን የሚመለከቱትን በመውሰድ ተግባራዊ በማድረግ ኮርፖሬሽኑ ግዴታውን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
ለአብነትም አንድ ባቡር በፊት ከነበረው የመጫን አቅም 25 በመቶ ብቻ የሚሆን ተሳፋሪ በመያዝ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልፀው፤ በዚህም አንድ ባቡር 64 ሰው ብቻ የሚጭን መሆኑን ቅጥያ ካለው ደግሞ 128 ተሳፋሪዎችን የሚጭን መሆኑን ገልፀዋል።
ተሳፋሪዎች ትኬት ሲቆርጡም ሆነ ወደ ባቡር ሲገቡ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ማድረግ ግዴታቸው መሆኑን ተናግረው፤ ይሄም ካለፈው ሚያዚያ ወር መጀመሪያ አካባቢ ጀምሮ ተግባራዊ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህንን በማስፈጸም በኩል ፖሊስ ድጋፍ እያደረገ ስለመሆኑም ገልጸዋል።
እጅ የመታጠቢያ የሳኒታይዘር ግብዓቶችም እንዲሁ ተሟልተው ተሳፋሪዎች ወደ ቧቡሩ ከመግባታቸው በፊት ተጠቅመው እንደሚገቡ እና በባቡር መነሻና መድረሻ ቦታዎች ላይ የፀረ-ተህዋሲ ርጭት እንደሚደረግም አብራርተዋል።
ይሄንን ለመቆጣጠር እንዲያስችል የኮርፖሬሽኑ ሰራተኞች፣ የፌዴራል ፖሊስ እና በጎ ፈቃደኞች በጋራ እየሰሩ መሆኑን እና እስካሁንም ውጤታማ መሆኑን አስረድተዋል።
አሁን ያለውን የትራንስፖርት እጥረት የወጡ መመሪያዎችን በትክክል ባለመተግበራቸው መሆኑን የጠቀሱት ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ ''ህብረተሰቡ ለአስገዳጅ ጉዳይ ካልሆነ በቀር እንቅስቃሴ ቢቀንስ መልካም ነው'' ብለዋል።
ወረርሽኙን የመከላከል ጥረቱ ውጤታማ እንዲሆን የወጡ መመሪያዎችን ህብረተሰቡ ሳይሸራርፍ በአግባቡ እንዲተገብርም ጥሪ አስተላልፈዋል።